ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን በአዲስ አበባ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ መንግሥት ደርሶላቸው ቅብዓተ መንግስቱም ተፈጽሞላቸው ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ተብለው ዘኢትዮጵያ ተብለው የነገሡበት ቀን ነበር፡፡
እንደ ኒውዮርክ ታይምስ የዘመኑ ዘገባ የበዓለ ሲመቱ ዝግጅት ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የፈጀ ሲሆን ከመላው ዓለም የተጋበዙ ልዑላንና የመንግስታት ተወካዮች የተገኙበት ነበር፡፡
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በዓለ ሲመት በኋላ 91 ዓመቱን ሊደፍን አንድ ወር ብቻ በቀረው ታሪካችን የመጀመሪያው ሊሆን የሚችለው የሀገር መሪ በዓለ ሲመት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በአማረ ሁኔታ ተድሶ በተጠናቀቀው ታሪካዊው የመስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራት መሪዎችና የመንግሥታት ልዑካን በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
ከ2008 ዓ.ም በኋላ እየጋመ ለመጣው ሀገራዊ ተቃውሞ ጆሮ መስጠትና መፍትሔ መፈለግ ተስኖት ሲናጥ የከረመው የጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሣለኝ መንግሥት ለውጡን ለማዋለድ ወስነው ሥራቸውን በራሳቸው ፈቃድ በለቀቁት አቶ ኃ/ማርያም ደሣለኝ ምትክ ዶ/ር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን በማምጣት ሀገራዊውን ችግር ለመፍታት አዳዲስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችንና ተስፋዎችን ይዞ የለውጥ ጉዞው ተጀመረ፡፡
ብዙ ተስፋን በሰነቀው የለውጥ ሂደት ከጅምሩ ነባሩን ድርጅታቸውን አፍርሰው ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ወስነናል ያሉት ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ ወደ ተግባር ሲገባ እንደቃላቸው ተስማምተው መፈጸም አቅቷቸው ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹን በበላይነት ሲመራ የነበረው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አመራሮች አዲስ የተመሠረተውን ሀገራዊ ፓርቲ ላለመቀላቀል በመወሰን በክልላቸው ያላቸውን ይዞታ ማጠናከርና ከለውጡ ሂደት በተጻራሪ መቆማቸው ግልጽ እየሆነ ሄደ፡፡
በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ወጥ በሆነና በተመጣጣኝ ውክልና ተመሥርቶ በክልልና በፌደራል ደረጃ በኢህአዴግ እግር የተተካውና ሀገሪቱን ወደ ሰላምና ብልጽግና በማሻገር አዲስ ምዕራፍን እከፍታለሁ ያለው ብልጽግና ፓርቲ ገና ከጅምሩ በርካታ ተግዳሮቶችን እያስተናገደ፣ እየሰፉና መልካቸውን እየቀየሩ በመጡት ቀውሶች እየተናጠ፤ የሰነቀውን ተስፋ በሚያጨልሙ፣ የነበረውን ድጋፍና አመኔታው ጥያቄ ውስጥ በሚያስገቡ ሁነቶች ተሰንጎ ቆየ፡፡
የዶ/ር አቢይ የለውጥ አመራር በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ ቃል በመግባት የእስር ቤትና የሀገሪቱን በር እየከፈተ ወደ ሰላማዊው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመለሳቸው ተፎካካሪዎችና ለራሱ ለብልጽግና ፓርቲም ሌላ ፈተና የሆነው ደግሞ ዓለም አቀፋዊ የጤና ሥጋት ሆኖ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተስፋ የተጣለበት ምርጫ መራዘሙ ነበር፡፡
የምርጫውን መራዘም ምክንያት በማጣጣል የለውጡን አመራር በኢሕገመንግስታዊነት የከሰሰው ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የነበረው ሕወሓት በራሱ ሥልጣን የተናጠል ምርጫ ቢያካሂድም በፌዴራል መንግሥቱ ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ እየተካረረ በመጣው ልዩነት ሳቢያ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈጸመው ጥቃት መነሻነት ሕግ ለማስከበር የተገባበት ጦርነት ክፍተኛ ዋጋ ያስከፈለና በማስከፈል ላይ ያለ የሀገሪቱንም ቀጣይነት የተፈታተነ ክስተት ነበር፡፡
ኢትዮጵውያን በሚታወቁበት የፈተና ጊዜ አንድነትና ሕብረት ልዩነታቸውን ወደ ጎን በማለት ያጋጠመውን ሀገራዊ ፈተና ለመቋቋምና በጋራ ለመመከት ከመንግሥት ጎን በመቆማቸው የተደቀነውን ችግር ለመቆጣጠር ወደ መቃረቡ እንዲደረስና በዚህ ሁሉ ፈተናም መሀል ምንም እንኳ ከችግር የጸዳና እንከን አልባ ባይሆንም ለመጪው ጊዜ ተስፋን ያመላከተና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ በጎ ጅምሮች የታዩበት ሰላማዊ ምርጫ ለማከናወን ተችሎ ብልጽግና ፓርቲ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን አብዛኛውን ድምጽ አግኝቷል፡፡
ከሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ትግራይና ከተወሰኑ የደቡብ ክልል አካባቢዎች በስተቀር የመጀመሪያው ምርጫ በተደረገባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አብዛኛውን ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ሰሞኑን በየክልሎቹና በከተማ አስተዳደሮቹ የመንግሥት ምሥረታውን ያከናወነ ሲሆን በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልልና በደቡብ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችንም ጭምር በካቢኔ ውስጥ በማካተት አሳታፊ መንግሥት ለመሆን ያለውን ዝግጁነት አመላክቶበታል፡፡
የዚህ ሁሉ መካተቻ የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ምሥረታም አዲስ ምዕራፍ በሚል መርሕ በቅርቡ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓተ ንግሥ ወዲህ እጅግ ከፍተኛ ዝግጅት በተደረገትና ደማቅ በሆነ ሥነ ሥርዓት የአፍሪካ ርእሳነ መንግሥታትና ከፍተኛ ልዑካን እንዲሁም የሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አመራሮች፣ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ተሳታፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶቻቸውን በኢትዮጵያ ብቻ ለተከበሩ እንግዶች እንዲነጠፍ ተመርጦ በተዘጋጀው የአደይ አበባ ምንጣፍ እየተቀበሉ ያመሹት ዶ/ር አቢይ አህመድ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በማለዳው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው አዲስ በተመረጡት የሕዝብ እንደራሴዎች የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን የመጀመሪያው ስብሰባ በተከናወነ ሥነ ሥርዓት በብዙኃኑ እንደተጠበቀው በብልጽግና አጋራቸው አቶ ደመቀ መኮንን በዕጩነት ቀርበው ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንዲያገለግሉ በሕዝብ እንደራሴዎቹ ተሹመው በቃለ መሀላ ኃላፊነቱን ተረክበዋል፡፡
ደረጃውንና ታሪኩን ጠብቆ እንደ አዲስ የታነጸው የመስቀል አደባባይ እንደ አደይ አበባ በደመቀውና አዲስ ተስፋን በሚፈነጥቀው ቢጫ ቀለም ባላቸው ጨርቆችና ሪቫኖች ተውቦ ባማረ የመድረክ ግንባታ እንግዶቹን ሲጠባበበቅ የነበረ ሲሆን መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት ዶ/ር አቢይ እንግዶቻቸውን አስከትለው በቦታው ሲደርሱ በስፍራው በተሰበሰቡት እንግዶችና የበዓለ ሲመቱ ታዳሚዎች የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
የዑጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቪኒ፣ የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫኪር ማያርዲት፣ የሴኔጋሉ ማኪ ሳል፣ የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ፣ የጅቡቲው ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፣ የሶማሌው አብዱላሂ ፎርማጆና የናይጄሪያው ሙሀመድ ቡሃሪ በሥርዓተ ሲመቱ ላይ የተገኙ ፕሬዝዳንቶች ሲሆኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን በንግግር አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራን አፋጦ የነበረው የድንበር ጉዳይ በወንድማማችነት መንፈስ ከተፈታ በኋላ ለኢትዮጵያና ለዶ/ር አቢይ አህመድ ዋነኛ ወዳጅና አጋር መሆናቸውን በተደጋጋሚ ጉብኝትና ትብብር እያረጋገጡ የመጡት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሥርዓተ ሲመቱ ላይ አለመገኘታቸው ግን አነጋጋሪ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም፡፡
የዑጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ከመልካም ምኞታቸው ጋር አያይዘው በዑጋንዳ የጎሣና የሃይማኖት ክፍፍል ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረ በመግለጽ የማንነት ፖለቲካ የሚፈጥረውን ልዩነት መቅረፍ ወደ ለውጥ ጎዳና እንደሚያሻግር ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ነጻነቷን የተጎናጸፈችው የታዳጊዋ ሀገር የደቡብ ሱዳኑ ማያርዲት ሳልቫኪር ዐፄ ኃይለ ሥላሴ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያምና እስከ ዶ/ር አቢይ ያሉት መሪዎች ለደቡብ ሱዳን ነጻነት የተጫወቱትን ገንቢ ሚና በአድናቆትና በምስጋና አውስተው “ታላቅ እናታችን የሆነችው ኢትዮጵያ እኛ ባለፍንበት ችግር እንድታልፍ አንፈልግም” ያሉ ሲሆን “በምትሄዱበት መንገድ ሁሉ አብረናችሁ ነን” በማለት ልባዊ አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ የአፍሪካ የነጻነት እናት መሆኗን አጉልተው የተናገሩት የኬኒያው መሪ ኡሁሩ ኬኒያታ “የሁላችን እናት እንደመሆኗ የሰላሟ መረበሽ የሁሉንም ሰላም ያውካል” በማለት ኬኒያ የኢትዮጵያን እድገትና ሰላም ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሀመድ ቡሃሪም “የሰኔው ምርጫ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ያላቸው ጥልቅ ፍላጎት ማሳያ እንደሆነ አምናለሁ” ብለው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ አንድነታቸውና ሉዓላዊነት በሕብረት እንዲቆሙ አሳስበዋል፡፡ የጅቡቲው ኢስማኤል ኦማር ጊሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቀድሞ ታላቅነቷን እንድታድስና ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም ሆና ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ያበቃቸውን ፈጣሪን በማመስገን የበዓለ ሲመት ንግግራቸው የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዚህ ወሳኝና ፈታኝ ወቅት በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ የተቃጣውን ይህልውና አደጋ ለመቀልበስ በዱር በገደሉ፣ በቁር በሐሩሩ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ለሚገኙት ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት፣ ለመላው የፀጥታ አካላትና ለሕዝባዊው ኃይል ያላቸውን ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያውያንን ጽናት፣ አይበገሬነትና አትንኩኝ ባይነት ኩራታቸውና መመኪያቸው መሆኑን የገለጹት ጠ/ሚ አብይ ለሕዝቡ ያላቸውን ክብርና አድናቆትም ገልጸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጎን በችግሯ ጊዜ አብረዋት ለቆሙት በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉም በሕዝቡና በመንግሥታቸው ስም ምስጋናቸውን አድርሰዋል፡፡
የኢትዮጵያን ገናናነት ከታሪክ ገጾች አለፍ አለፍ እያሉ የጠቀሱት ጠ/ሚሩ “በቀደሙ ድሎቻችን ከሚሰማን የኩራት ስሜት ጋር ሲነጻጸር ነገ ላይ የሚጠብቀን ተስፋ ቢበልጥ እንጅ አያንስም” በማለት መጪው ጊዜ የተሻለና ብሩህ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመርከብ የመሰሉት ዶ/ር አቢይ “የዘመናት በጎ ድምር ውጤቶችን አጎልብተን ኢትዮጵያ የተባለችውን መርከብ ሞተሯን አድሰን፣ ማዕበል ወጀቡ ፈጽሞ እንዳያናውጣት አንጸን መልህቋን ሰብስበን ጉዘዋን ማስጀመር የኛ ድርሻ ሲሆን ለዘለቄታው በጽናት እንድትጓዝ ማድረጉ ደግሞ የየትውልዱ አደራ ይሆናል” ብለዋል፡፡

ጠ/ ሚኒስቴሩ ለዕለቱ በዓለ ሲመት ያበቃቸውን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ “ከእንከኖች ሁሉ የጸዳና የምኞታችንን ያህል እጅግ የተሳካ ነበር ባይባልም የዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመትከልና የማጽናት ህልም እውን ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፤ አንድ እርምጃም ወደፊት አራምዶናል” በማለት የገለጹት ሲሆን በምርጫው የተመዘገበውን ስኬትም “ድሉ የአንድ ፓርቲና የመንግሥት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ኢትዮጵውያንም እንደ ህዝብ ያሸነፍንበት እንደሆነ ተገንዝበን ይህን አጋጣሚ እነደ ሀገር በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ካዋልነው ብዙ ቀዳዳዎችን መድፈን የሚያስችል ትልቅ ዕድል ነው” በማለት አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር አብይ መንግሥታቸው በሁሉም፣ ከሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ህልም ለስኬት እንዲበቃ አሳታፊና አካታች አካሄድ ለመከተል አጥብቆ የሚሠራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን “ለዘመናት እየተከማቹ የመጡትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮችን በአንድ ፓርቲ መሪነትና መፍትሔ አፍላቂነት ብቻ ጨርሶ ማስወገድ ስለማይቻል ተደራርበው የመጡብንን ችግሮች ተባብረን ለማሸነፍ መነሳት ይኖርብናል” በማለት የአብረን እንሥራ ይፋዊ ጥሪያቸውንም አቅርበዋል፡፡
“የፖለቲካ ሥርዓቱ የአሸናፊዎች ፍላጎት ነጸብራቅ ብቻ ሳይሆን የመግባባት ውጤትም እንዲሆን አበክረን እንሰራለን” ያሉት ጠ/ሚ አብይ በፖለቲካው ያለውን ልዩነት ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለማካሄድና የምክክር ሂደቱም ችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታሉ ብለው የሚያምኑትን ሁሉ የሚያካትት፣ በፖለቲካ ልሂቃኑ ብቻም ሳይሆን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍና ሀገር በቀል መፍትሔንም ታላሚ ያደረገ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የገጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ ለማለፍ በቀጣይም ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር እንድትችል ትክክለኛ አቋምና የተሟላ አቅም ያለው የፀጥታና ደህንንት ኃይል እንደምትገነባ የገለጹት ጠ/ሚኒስተሩ ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ የወዳጆቸዋን ድጋፍ አጥብቃ እንደምትሻ ነገር ግን ማንኛውም ወዳጅነት የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ሊሠዋ በሚችል መልኩ ሊሆን እንደማይችል አጽንኦት በመስጠት ኢትዮጵያ ለውጭ ጣልቃ ገብነትና ተጽእኖ እንደማትንበረከክ አስገንዝበዋል፡፡
ለወንድምና እህት አፍሪካውያንም “ኢትዮጵያ ለአፍርካዊ ችግሮች አፍርካዊ መፍትሔ በሚል መርሕ የተባበረችና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ብሎም በዓለም መድረክ ጥቅሟን የምታስጠብቅ አህጉር እንድትኖረን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነቷን ለመወጣት ትሰራለች” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የተጀመረውን የታላቁ ሕዳሴን ግድብ ማጠናቀቅ፣ የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠርና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ኢኮኖሚውን በብዙ ዘርፎች የተዋቀረ፣ ብዙ ተዋናዮች ያሉትና ብዙዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሆን መስራት፣ የዜጎችን ምሬትና መንገላታት የሚቀርፍ ግልጽና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥና ምቹ የሕዝብ አስተዳደር እንዲኖር፣ ሌብነትን እንደ ከፍተኛ የደህንነትና የህልውና አደጋ በማየት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዲሁም የለውጡን መልካም ጅምሮች አጠናክሮ ማስቀጠል የመንግስታቸው ትኩረት መሆኑን ገልጸው እንደተለመደው ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ብለው መልዕክታቸውን አጠቃለዋል፡፡
በበዓለ ሲመቱ ላይ የፀጥታ ኃይሉ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ የአሥሩ ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮች ትርዒት በማቅረብና ሠላምታ በመስጠት በክብር እንግዶቹ ፊት በሰልፍ አልፈዋል፡፡
በበዓለ ሲመቱ መርሐ ግብር ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካቢኔያቸውን በዕለቱ አቅርበው ያላጸደቁ በመሆኑ በቀጣይ ቀናት በምክር ቤቱ ቀርበው የሚያዋቅሩትን ካቢኔ ዕጩዎችም አቅርበው የሚያሾሙ ሲሆን አስከዚያው ድረስ ተፎካካሪ ፓርቲዎችንና በተለያየ ዘርፍ አቅም ያላቸውን ግለሰቦች በሥራ አስፈጻሚው ውስጥ ለማካተት ብልጽግና ፓርቲ በያዘው ዕቅድ መሠረት የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና ታዋቂ ሰዎች የሰሞኑ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]

