የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የህዳሴው ግድብ ድርድር በአራትዮሽ ይመራ በሚል ለዓለም አቀፍ ተቋማት ደብዳቤ መፃፋቸውን ኢትዮጵያ ወቀሰች
ከሰሞኑ ሱዳን የህዳሴው ግድብ በአውሮፓ ህብረት ፣ በአሜሪካ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ይከናወን በሚል ደብዳቤ መፃፏን ተከትሎ የኢትዮጵያ አቋም ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በጋዜጠኞች ተጠይቀው ነበር።
አምባሳደሩ "ይህን ጉዳይ በተመለከተ ይፋዊ መረጃ አልደረሰንም። እንደሚታወቀው በሶስትዮሽ ድርድር ውስጥ አሜሪካና አውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች ናቸው ። ከወራት በፊት የታዛቢዎች ሚና ከፍ ይበል የሚባል ሃሳብ ሲቀርብ የተቃወመችው ግብፅ ናት። ቀጥሎ ኮንጎ የድርድር ማስተባበር ታከናውን ተብሎ ይህንን ስንቀበል አሁን ደግሞ አደራዳሪዎች አራት ይሁኑ የሚል መረጃ እየሰማን ነው። ይሁን እንጂ በይፋ መረጃ አልመጣልንም። ነገርግን በመርህ ደረጃ ድርድሩ በሶስታችን አገራት የሚከናወን መሆን እንደሚገባውና ጠቃሚው አካሄድም ይህ መሆኑን ነው የምናምነው። እኛ ድርድሩ በመስፋትና መጥበቡ ላይ ችግር የለብንም። ነገር ግን ትልቁ ጉዳይ የሶስታችን አገራት መሆኑ ነው የበለጠ ጠቃሚው።" ሲሉ ተናግረዋል አምባሳደሩ።

አያይዘውም "የሱዳን መሪዎች አሁን እያደረጉ ያለው በተለይ መሬታችንን መውረራቸው ልክ አይደለም።" ያሉት ቃል አቀባዩ ለሱዳንና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመው የሁለቱ አገራት ጥንታዊ ወዳጅነት ነው ብለዋል።
አምባሳደር ዲና በዛሬው መግለጫቸው ዲፕሎማቶች በትግራይ ጉብኝት ማድረጋቸው በትግራይ ክልል ጉዳይ በምዕራብ አገሮች እየተደረገ ያለው ጫናና የተሳሳተ ግንዛቤ እንደሚቀይረው እምነታቸውን ገልፀዋል።
" የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ አውሮፓ ህብረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየለዘበ ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ' ትግራይ እንግባ ' አሉ፡ ፈቀድን ፤ 'ሰብአዊ መብት ጥሰትና የሴቶች መደፈር አለ' አሉ በገለልተኛ ወገን እናጣራ ብለን ፈቀድን፣ 'ድጋፍ ጠንክሮ ይቀጥል' አሉ ፡ እነሱ ባይሉንም የትግራይ ህዝብ ህዝባችን በመሆኑ አጠናክረን እየደገፍን ነው። 4.2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ አድርገናል። ስለሆነም እነዚህ ሁሉ በተፈቀደበት አሁን እውነቱን እየተደረዱ ነው። ይሁንና ግለሰቦችና አንዳንድ ሚዲያዎች ማዛባታቸውን እየቀጠሉ ነው። ቀጠናውን በመረበሽ ጥቅም እናገኛለን የሚል ና የህወኃት ፕሮፓጋንዳ ሰለባዎች አሁንም አሉ" ብለዋል።
አምባሳደሩ አውሮፓ ህብረትና አሜሪካ እውነቱን እየተገነዘቡ የአቋም ለውጥ እንደሚያደርጉ ምልክቶችን እያየን ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ በመግለጫው ሌላው ትኩረት የሰጡት ጉዳይ በአየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር መጠራትን በተመለከተ ነው። " አየርላንዶች በነ ጌልዶፍ ዊ አር ዘወርልድ ብለው እንዳልደገፉን ዛሬ ግን ወቅቱን ያላገናዘበ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል። በፀጥታው ምክር ቤት ስለኢትዮጵያ ጉዳይ እየሰሩ ያለው ነገር እንደ አገር አስከፍቶናል። አምባሳደሯን ኢትዮጵያ የጠራችው ለዚህ ምክክር ለማድረግ እንጂ ኤምባሲዋን አልዘጋችም።" ብለዋል።
በየመን ሰንዓ እስር ቤት በደረሰው የእሳት አደጋም ህይወታቸው ካለፉት 43 ሰዎች መካከል ኢትዮጵያን እንዳሉበትና በሞቱት ወገኖች ማዘናቸውን የገለፁት አምባሳደሩ ስርዓተ ቀብራቸው በዚያው መፈፀሙንም ገልፀዋል። ከሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ብቻ 888 ዜግች በሳምንቱ መመለሳቸውንም አንስተዋል።
በአሜሪካና አውሮፓ አገሮች ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ወግነው ያካሄዱት የድጋፍ ሰልፍም የሳምንቱ አበረታች ክስተት እንደነበር በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

