የጥቅም ወጋገን ወይስ የታሪክ ጥላ?
በየካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ረጅፕ ጣይብ ኤርዶጋን አዲስ አበባን በረገጡበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሰማይ ላይ አዲስ ወገግታ የታየ መሰለ። ሁለቱ ሀገራት በኢነርጂ ትብብር ላይ የመግባቢያ ስምምነት ሲፈራረሙ፣ በአዲስ አበባ አየር ላይ የጋራ ተጠቃሚነት ስሜት ነግሶ ነበር።
ቱርክዬ በሶማሊያ ወታደራዊ ካምፕ መመስረቷና በ‘አንካራ ሂደት’ (Ankara Process) ቀጠናዊ ድርድሮችን ማመቻቸቷ፣ ተጽዕኖዋ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስር እየሰደደ መሆኑን ያሳያል።
ይሁን እንጂ፣ 'ከሰማይ የወረደ ሁሉ ለበረከት አይደለም' እንደሚባለው፤ እነዚህ ስምምነቶች የራሳቸው የሆነ የጂኦፖለቲካዊ ዋጋ (Price Tag) እንዳላቸው እሙን ነው።
እንዲያውም በዛሬዋ የአፍሪካ ቀንድ፣ አሮጌ ታሪኮች አዲስ ጭምብል ለብሰው የሚመጡባቸው መድረኮች መብዛታቸው አይካድም።
የመንግሥት ደጋፊዎች ጉብኝቱን እንደ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል አከበሩት—ቱርክዬን ወደ አጋርነት መሳብ የኢትዮጵያን ጂኦፖለቲካዊ ጡንቻ እንደሚያፈርጥ በማመን።
በአንጻሩ የተቃዋሚ ወገኖች ስምምነቱን እንደ ስውር ዲፕሎማሲያዊ ማስጠንቀቂያ ተመለከቱት—አንካራ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገው ጥረት፣ የኢትዮጵያን ክንድ ለመገደብ የታለመ ሊሆን እንደሚችል በመስጋት።
ሆኖም የሁለቱም ወገን ትረካዎች በወቅታዊው የፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ ማዕቀፍ ውስጥ የታጠሩ ናቸው። ያንን ረጅሙን የታሪክ ጉዞ ግን ማንም ልብ ያለው አይመስልም።
በፈገግታ የታጀበው የእጅ መጨባበጥ በስተጀርባ የቆመውን የአምስት መቶ ዓመታት የታሪክ መንፈስ ያስተዋለ የለም።

የአንካራ ረጅም እጆች
አንካራ ከአዲስ አበባ በግምት 3,500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። በመካከላቸው በርካታ ሀገራትና ሰፊ መልክዓ ምድር ቢኖርም፣ የኦቶማን ጥላ ግን ኢትዮጵያ ላይ በጉልህ እንዳጠላ ነው። ኦቶማን ቀድሞውኑ የሜዲትራኒያን እና የጥቁር ባህር ባለቤት እና የባህር በር ፍለጋ "ጠኔ" የሌለባት ሀገር ናት።
ሆኖም ግን፣ ወደቡን ለማትዋሰነው ቀይ ባህር ያላት ጥልቅ ጉጉትና ጣልቃ ገብነት ላለፉት አምስት ክፍለ ዘመናት ሳያቋርጥ ቀጥሏል።
እዚህ ላይ የሮማውያኑን "ባህርን የገዛ ዓለምን ይገዛል" ዝነኛ አባባል አንካራ የተረዳች ይመስላል። ከኦቶማን የባህር መርከቦች እስከ ዳህላክ ደሴቶች ምሽጎች፣ ከጥንታዊ የባህር መድፎች እስከ ዛሬው ዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ሽምግልና ድረስ፣ ስልታዊው መስመር ሳይቋረጥ ዘምኗል።
አንካራ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያውን ኤምባሲዋን በ1926 እ.ኤ.አ. በአዲስ አበባ መክፈቷ፣ እንዲሁም በ1985 ዓ.ም. የኤርትራን ነፃነት በመቀበል ረገድ ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፏ በአካባቢው ላይ ያላት ስትራቴጂካዊ ፍላጎትና ጣልቃ-ገብነት ዘመን አይሽሬ መሆኑን ይመሰክራሉ።
በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ‘ወደ አፍሪካ መከፈት’ (Opening to Africa) የተሰኘ ፖሊሲ መንደፏ፣ ተፅዕኖዋ በአህጉሪቱ ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየገነነ መምጣቱን የሚያሳይ ግልጽ ማሳያ ነው።
ዛሬ አንካራ በአፍሪካ ቀንድ ያላት መገኘት በወረቀት ላይ ካለ ስምምነት የዘለለና መሬት የረገጠ ነው።
በሞቃዲሾ የገነባችውና ከሀገሯ ውጭ ትልቁ የሆነው "ቱርክሶም" (TURKSOM) ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ፣ በጂቡቲ በኩል ያላት የንግድ ቀጠና ተሳትፎና በኤርትራ አሰብና ምጽዋ ወደቦች ላይ ያላት የታሪክ ተሳትፎ ፍላጎት፣ ቱርክዬን የቀጠናው ቁልፍ ተዋናይ አድርጓታል።
የሀገሪቱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የባቡር መስመር ዝርጋታና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው ድርሻ ደግሞ ይሄው ርቀት ያልገደበው ተፅዕኖ ከባህር ዳርቻ አልፎ እስከ ሀገሪቱ እምብርት መዝለቁን ያረጋግጣል።
በአጠቃላይ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቱርክዬ መገኘቷ ድንገተኛ ክስተት ሳይሆን፣ ጥንታዊው የታሪክ ፍላጎት ዘመናዊ መልክ ይዞ መመለሱ ነው።
የጂኦግራፊ እስረኝነት እና የባህር በር ናፍቆት
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “የባህር በር የህልውና ጉዳይ ነው” የሚለውን መርህ ደጋግመው ከማስተጋባት አልፈው፣ አጣዳፊነቱንም በአንክሮ እያስገነዘቡ ይገኛል። የሚገርመው ግን፣ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ብቻ የቀይ ባህር ጉዳይ በሦስት መሪዎች ዘንድ ሦስት ዓይነት ትርጓሜዎችን አስተናግዷል፦
በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን የሀገሪቱ 'ወሳኝ አንገት' ተብሎ የተቆጠረው ባህር፤ በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን ወደ ተራ 'የግመል ውኃ ማጠጫነት' ወርዶ ሰንብቷል፤ ዛሬ ደግሞ በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዳግም እንደማይተካ 'የህልውና እስትንፋስ' እየተቀነቀነ ይገኛል።
የታዋቂው ወታደራዊ ስትራቴጂስት ናፖሊዮን ቦናፓርት “የአንድ ሀገር ፖለቲካ የሚወሰነው በጂኦግራፊዋ ነው” የሚለው ጥቅስ እዚህ ላይ በጉልህ ይደመጣል።
ከኢትዮጵያ ተራራዎች አናት ላይ ሆኖ የባህሩን ጨው ማሽተት ይቻላል፤ በካርታ ላይ ያለው ርቀት እጅግ አጭር ቢመስልም፣ ላለፉት አምስት መቶ ዓመታት ግን ባህሩ ለኢትዮጵያ “የቅርብ ሩቅ” ሆኖባት ቆይቷል።
ዛሬ ዛሬ በእንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ቲም ማርሻል ‘የጂኦግራፊ እስረኝነት’ (Prisoners of Geography) ተብሎ የተሰየመው ጽንሰ-ሃሳብ የወቅቱን ፖለቲካዊ አየር እየናኘው ይገኛል። ይህ እሳቤ ኢትዮጵያን “በሮች በሌሉበት ክፍል ውስጥ የታሰረች ግዙፍ ሀገር” አድርጎ ይስላታል።
የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ቀጥተኛ መስመር ሳይሆን ራሱን የሚደግም ዑደት (Loop) ይመስላል። የታዋቂው ደራሲ ማርክ ትዌይን አባባል እዚህ ላይ በሚገባ ይገጥማል፦ “ታሪክ ራሱን አይደግምም፤ ነገር ግን ይገጥማል (Rhymes)።”
በትናንቱ ታሪክ የኃይል ሚዛኑን የደፋው የኦቶማን ነፍጥ (Musket) ሲሆን፣ በዛሬው የታሪክ ምዕራፍ ደግሞ የባይራክታር ቲቢ2 (Bayraktar TB2) ድሮኖች በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ መታየታቸው የጦርነቱን አቅጣጫ በመቀየር ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ዘመናቱ ቢቀየሩም፣ ቴክኖሎጂው ቢሻሻልም፣ በስትራቴጂካዊ ገበያው ላይ ያለው "ነጋዴ" ግን ያው ራሱ መሆኑን ይህ ሐቅ ያስገነዝበናል።
ነገር ግን እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ የማይጠየቅ አንድ ወሳኝ ጥያቄ አለ፤
ይህ “እስር ቤት” መሃንዲስ አልነበረውም?
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ከባህር እንድትነጠል መሰረቱን የጣለውና ለዛሬው ወደብ አልባነታችን ዋነኛ ምክንያት የሆነው ኃይል ማን ነው?
መልሱ በቀጥታ ወደ ዛሬዋ ቱርክዬ ቀዳሚ ወደሆነው የኦቶማን ኢምፓየር ይመራናል።
መድፎች በባህር ዳርቻ፦ የባሩድ ቅጥር
በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የኦቶማን ስትራቴጂ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የታቀደና በባህር ኃይል የበላይነት ላይ የተመሰረተ ነበር። የባላንጣቸውን የፖርቹጋልን መስፋፋት ለመግታት፣ የኦቶማን ባለሥልጣናት ቀይ ባህርን ዋነኛ መፋለሚያ ስፍራ አደረጉት።
በቀይ ባህር ዳርቻ የሚገኙ ኃይሎችን በዘመናዊ መሣሪያ በማስታጠቅም የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣንና ሉዓላዊነት እጅግ ፈታኝና ሰቆቃ የበዛበት አድርገውታል።
ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደዘገቡት፣ እንደ ሐረሩ ማህፉዝ ያሉ ኃይሎች በዘይላ ላይ ስልታዊ በሆነ መልኩ እንዲመሸጉ ተደርጓል። በዚህም ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ከባህር ዳርቻ ምሽጎች ወደ መሃል ሀገር ግጭቶች ይፈሱ ነበር።
በአፄ ልብነ ድንግል ዘመን፣ በኦቶማን በኩል ያለማቋረጥ የሚቀርበው የጦር መሣሪያ የአህመድ ኢብን ኢብራሂም አል-ጋዚን (ግራኝ አህመድ) ዘመቻ በማጠናከር፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ እልቂት፣ ለንብረት ውድመትና ለቅዱሳን መካናት መውደም ምክንያት ሆኗል።
ይህም በ1521 ዓ.ም. በሽምብራ ኩሬ ጦርነት ወቅት የኃይል ሚዛኑን በማዛባት፣ ንጉሡ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እንዲያፈገፍጉ አስገድዷቸዋል። በውጤቱም የቀይ ባህር ዳርቻ በኦቶማን ባሩድ የታጠረና ለደጋው መንግሥት ዝግ የሆነ ወደብ ለመሆን በቅቷል።
ቆይቶም በአፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን፣ የኢትዮጵያ ጦር የኦቶማን ወታደሮችን ከኤርትራ ምድር ለማስወጣት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል። በ1581 ዓ.ም. የተደረጉት ዘመቻዎች ወራሪውን ኃይል ወደ ቀይ ባህር ዳርቻ ገፍተውት የነበረ ቢሆንም፣ ተፈጥሮ ግን ጣልቃ እየገባች ሂደቱን እጅግ ፈታኝ አድርጋዋለች።
የአፋር በረሃና ዝቅተኛው የባህር ዳርቻ ስፍራዎች ለደጋው ተዋጊ ትንፋሽ የሚያሳጥሩ የንዳድ ምድሮች ነበሩ። ተፈጥሮ ራሷ የኦቶማን ታማኝ አጋር የሆነች ይመስል፣ የደጋው ጦር በሙቀቱ ሲዝል የባህር ዳርቻው ኃይል ዳግም ያገግም ነበር።
ኦቶማኖች ዱላ ሲበረታባቸው ወደ ባህር ምሽጎቻቸውና ወደ ዳህላክ ደሴቶች እያፈገፈጉ፣ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ደጋው ሲመለስ ደግሞ ዳግም ወደቡን እየተቆጣጠሩ የአይጥና ድመት መሰል ጨዋታ ይጫወቱ ነበር።
ይህ ስልት ኢትዮጵያውያን የተሟላ ድል እንዳይቀዳጁ ዋነኛ መሰናክል ሆኖ ዘልቋል። ያ ጂኦግራፊያዊ ሚዛን-አልባነትም ለዘመናት ጸንቶ የቆየ ሲሆን—እስከ ዛሬም በቴክኖሎጂ ያልተፈታ የተፈጥሮና የፖለቲካ 'ቁልፍ' ሆኖ ቀጥሏል።
የኢስታንቡል ጥላ፦ ተረት፣ እምነት እና ቃና
የቱርክዬና የኢትዮጵያ ቁርኝት በዲፕሎማሲያዊ ቀለም ከመፈረሙ ከረጅም ዘመናት በፊት በእምነት ክር የተሰካ ነው። ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ በአይነ ሕሊናቸው የሐዋርያው ጳውሎስን የጉዞ ፈለግ በአናቶሊያ ምድር ይከታተላሉ፤ የኖህ መርከብ ያረፈችበትን የአራራት ተራራንም በናፍቆት ይመለከታሉ።
ሙስሊሞችም በተራቸው የኢስታንቡል ጥንታዊ መስጊዶችና የኦቶማን ኸሊፋዎች በታሪክ የነበራቸውን መንፈሳዊ ተፅዕኖ በክብር ያስታውሳሉ።
ይህ መንፈሳዊ ትስስር በተጋራው ተረታተረት ይበልጥ ይጎለብታል፤ የናስረዲን (Nasreddin Hoca) አስቂኝና ጥበብ ያዘሉ ታሪኮች ለኢትዮጵያውያን ሕፃናት ለረጅም ጊዜ የሥነ-ምግባር መመሪያ ሲሆኑ ቆይተዋል።
ይህም የቱርክዬ ጥበብ በቴሌቪዥን መስኮቶች ከመታየቱ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ የሀገሪቱን የሕይወት ፍልስፍና የኢትዮጵያውያን የልጅነት ጓደኛ አድርጎታል።
ዛሬ ግን ይህ ተጽዕኖ ከጦር አውድማ አልፎ እስከ እልፍኝ ድረስ ዘልቋል። የቱርክዬ ድራማዎች በአማርኛ ተተርጉመው የኢትዮጵያን የቴሌቪዥን መስኮቶች መቆጣጠር ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለብዙ ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች ከጎረቤት አፍሪካ ከተሞች ይልቅ የኢስታንቡል ሰፈሮች ይበልጥ የታወቁና ናፋቂ ሆነዋል።
እንዲያውም ድራማዎቹ ላይ ተጥደው የሚውሉ ወጣቶችን በማየት፣ እንደ "ቃና ቴሌቪዥን" ያሉ ጣቢያዎች ትውልዱን ወኔ አልባና የሌላ ባህል ጥገኛ አደረጉት ብለው የሚኮንኑም ጥቂት አይደሉም።
ቱርኮች 'አንድ ሲኒ ቡና ለአርባ ዓመት የሚዘልቅ ትዝታ ይኖረዋል' የሚል ምሳሌያዊ አባባል አላቸው። ቱርክዬ በድራማዎቿ እና በባህሏ አማካኝነት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የምታሳርፈው አሻራ በቀላሉ የማይጠፋ መሆኑ፣ ለጂኦፖለቲካዊ ግዙፍ ተፅዕኖዋም ምቹ መደላድል መፍጠሩን ለማረጋግጥ ሌላ እማኝ አያሻም።
የቤት ደባላችን፦ ከሶፋ እስከ ሰርጀሪ
ዛሬ ቱርክዬ ለኢትዮጵያውያን አጋር ብቻ ሳትሆን "የቤት ደባላችን" (Roommate) ሆናለች። የአንካራ እና ኢስታምቡል የቤት ዕቃዎች የአዲስ አበባ ሾው-ሩሞችን አጥለቅልቀዋል።
ብዙ ሸማቾች ከርካሽ አማራጮች ይልቅ በዲዛይንና በጥንካሬያቸው ምክንያት የቱርክዬ ምርቶችን ይመርጣሉ። ሌላው ቀርቶ ቱርክዬ ለፀጉር ተከላና ለፕላስቲክ ሰርጀሪ (Cosmetic Surgery) የኢትዮጵያውያን ቁንጮ መዳረሻ ሆናለች።
በጉልህ በሚታይ መልኩ ቱርክዬ ኢትዮጵያውያን ምን ላይ እንደሚቀመጡ፣ ምን እንደሚለብሱ፣ ምን እንደሚያዩ አልፎም መልካቸውን እንዴት እንደሚቀርጹ ተጽዕኖ እያሳደረች ትገኛለች። እንዲያውም ለበርካታ ዜጎች የቱርክዬ ሸቀጦች ተጠቃሚነት የኑሮ ደረጃ (Class) መገለጫ እየሆነ መጥቷል።
ለጉብኝትም ሆነ ለሸመታ (Shopping) የበርካታ ኢትዮጵያውያን ዋነኛ ምርጫ መሆኗ፣ አንካራ የመንግሥትን ቀልብ ብቻ ሳይሆን የዜጎችንም ልብ ጭምር እንደተቆጣጠረች ያሳያል።
ይህ የተቀናጀ ተጽዕኖ ውጤት ነው፡ "Hard power" (ድሮኖቹ) የመንግሥትን ዕድሜ ሲጠብቁ፣ "Soft power" (ድራማዎቹ) ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ምኞትና የቤት ውስጥ አኗኗር ከውስጥ ሆነው ይቀርጹታል። ድሮኑ በሰማይ ላይ፣ ሶፋው ደግሞ በሳሎን ውስጥ የዚሁ የተቀናጀ ስልት አካላት ናቸው።
የታሪክ ተቃርኖ
የቱርክዬ ስትራቴጂካዊ ምኞት ግልጽ ነው፤ በቀይ ባህር ላይ ንቁ ተሳትፎ!
የአንካራ ኮምፓስ ከኦቶማን መድፎች እስከ ባይራክታር ድሮኖች፣ ከጥንት የባህር ዳርቻ ምሽጎች እስከ ዘመናዊው የኢነርጂ ዲፕሎማሲ ድረስ አቅጣጫውን ስቶ አያውቅም።
ቱርክዬ የቆመችበትንና የምትፈልገውን ጠንቅቃ ታውቃለች፤ ጥያቄው ግን "እኛስ የት ነን?" የሚለው ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣትን "የህልውና ጉዳይ" እያለች፣ ይህ ታሪካዊ መገለል በማንና እንዴት እንደተጠነሰሰ ችላ ልትለው ትችላለች?
ያለ ታሪካዊ ግልጽነትስ እውነተኛ አጋርነት ሊያብብ ይችላል?
ለዛሬው ወደብ አልባነታችን የመጀመሪያውን ጡብ ያስቀመጠችው ይቺው ሀገር መሆኗ እየተዘነጋ፣ ዛሬ በቱርክዬ መጋረጃ በተዋቡ ሳሎኖቻችን ውስጥ ሆነን "የህልውና እስትንፋስ" መጠበቃችን ትልቅ የታሪክ ሽሙጥ ነው።
"በሬ ካራጁ" እንደሚባለው፣ ለታነቅንበት የጂኦፖለቲካ እስር ቤት ቁልፉን ከያዘው ወገን መፍትሔ መፈለጋችን ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
የኦቶማን መድፎች ጸጥ ካሉ ቆይተዋል፤ ዛሬ ግን በድሮን ድምፅና በቱርክዬ ቬልቬት ጨርቆች መካከል ሆነን አንድ ታሪካዊ እውነትን እናስተውላለን፦ ትላንት የባህር በራችንን የቆለፈው እጅ፣ ዛሬ “አጋር” ተብሎ ተመልሷል።
በትላንቱ ታሪክ በባህር ዳርቻዎችና በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ተወስኖ የነበረው የቱርኮች ተፅዕኖ፣ ዛሬ እስከ ቤተመንግስታችን፣ መደብሮቻችን፣ ሳሎኖቻችንና ሚዲያዎቻችን ዘልቆ ሁለንተናችንን ተቆጣጥሮታል።
የተመረጠ የታሪክ ትውስታ (Selective Memory)
ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው ምሁራን ስለ ጋራ ቅርስ ሲያወሩ፤ ትኩረታቸው በሐረሪዎች የኦቶማን የዘር ሐረግ፣ በአንካራ ዘመናዊ አጋርነትና ረዥም ዕድሜ ባስቆጠረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይ ብቻ እንዲያርፍ ይሻሉ። በዚህ ትረካ ውስጥ እውነት ቢኖርም፣ እውነቱ ግን “የተመረጠ” እና የአንድ ወገን ብቻ ነው።
በአንጻሩ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በቀይ ባህር ዳርቻ የተካሄደውን ወታደራዊ ጣልቃ-ገብነትና ኢትዮጵያን ለዘመናት ለዘለቀው የባህር በር ዕጦት የዳረገውን ሂደት መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት ሲያስታውሱት አይታይም።
ዛሬ ባለው ሁኔታ ወቅታዊውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መመቻመች ማውሳት የቀለለ መስሎ ይታያል። ጥንት በሮቻችንን የቆለፈውን ኃይል ዛሬ ማስታወስ ይከብዳል።
እኛ የወደፊት የታሪክ ግንባታችንን እያከናወንን ያለነው በዝምታ በተሸፈኑ የታሪክ ክፍተቶች ላይ ነው። ምናልባትም “የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን” ተብሎ ይሆን?
ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ የሌሎችን ሀገራት ሉዓላዊነት የደፈሩ መንግስታት ከቆይታ በኋላ ስህተታቸውን አምነው ይቅርታ የጠየቁባቸውና ካሳ የከፈሉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ለዚህም በርካታ የአውሮፓ ቀኝ ገዢዎች ለአፍሪካ ሀገራት ያደረጉትን ማስታወስ ይቻላል።
በራሳችን ሀገር እንኳ ጣሊያን በወረራ ወቅት የወሰደችውን የአክሱም ሐውልት መመለሷ፣ እንዲሁም እንግሊዝ ከአፄ ቴዎድሮስና ከሌሎች የታሪክ አጋጣሚዎች ጋር የተያያዙ ቅርሶችን ተመላሽ ማድረጓ ትልቅ ማሳያ ነው።
እነዚህን ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ፣ የዛሬዋ ቱርክዬ ቀዳሚ የሆነው የኦቶማን ኢምፓየር ኢትዮጵያን ወደብ አልባ በማድረጉ ረገድ የነበረበትን ታሪካዊ ሚና እንዲያውቅ ማስታወስና ተገቢውን ማስተካከያ እንዲያደርግ “በተፋቀርንበት” ወቅት ጥያቄ ማቅረብ ለምን አይገባም?
ይህ ጥያቄ በጠብ ሳይሆን፣ አንካራ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ሰፊ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖና "ረጅም እጅ" በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን መንገድ በወዳጅነትና በትብብር እንድታመቻች እንደ አንድ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት እንዳናቀርብ የሚያግደን ህግ እና እግድ ይኖርብን ይሆን?
በመጨረሻም፦ ጂኦፖለቲካ አይታደስም (Reset አይደረግም)፤ ይከማቻል እንጂ። አምስት መቶ ዓመታት ደግሞ ቀላል የማይባል የታሪክ ክምችት ነው። ያለፈው ታሪክ አልሞተም፤ ይልቁንም በሳሎናችን ውስጥ ተቀምጦ በትዝብት እያየን ነው።
ዳንኤል ካሳሁን (ፒ ኤች ዲ) በመሬት-ነክ ጉዳዮች የተለያዩ መጣጥፎችን የሚያበረክቱ ሲሆን በኦስተን / ቴክሳስ የጂኦስፓሻል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው daniel.kassahun@gmail.com ይገኛሉ፡፡

