የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውስትራሊያ የቀጥታ በረራ ጅማሮ ዕቅዱን በአውሮፕላን እጥረት ሳቢያ እስከ 2028 ማራዘሙን አስታወቀ

የታዘዙት የአውሮፕላን ግዥዎች ርክክብ ቀድሞ ከተሳካ ግን ከዚያ በፊት ሊጀመር እንደሚችል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጠዋል።

EAL Mesfin Tasew.png

Ethiopian Airlines Airbus A350-941 (L), Mr Mesfin Tasew, Group Chief Executive Officer of Ethiopian Airlines (C), and Globe Australia (R). Credit: Getty Images / D.Kebede

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በቅርቡ ወደ አውስትራሊያ ከአዲስ አባባ የቀጥታ በረራ እንደሚጀምር አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ በበረራ ኢንዱስትሪው እያጋጠመ ባለው የትላልቅ አውሮፕላኖች ግዥና ኪራይ እጥረት የተነሳ ዕቅዱን መከለሱን ገልጿል።

 ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 3 ቀን በስካይላይት ሆቴል በተሰጠው የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ወቅት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የአውሮፕላን እጥረት ትልቁ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

ለአየር መንገዱ የቀጥታ በረራ ስድስተኛ አኅጉር ተደርጋ የተያዘችው አውስትራሊያም በዚህ የተነሳ 'በቅርቡ የአገልግሎታችን ተደራሽ አትሆንም' ብለዋል፤ እስከ 2028 ድረስ ሊራዘም እንደሚችልም ጠቁመዋል።

 ዋና ሥራ አስፈጻሚው በግዥ ትዕዛዝ ላይ ያሉት ትላልቅ አውሮፕላኖቻችንን ቀድመን የምንረከብ ከሆነ ግን በፍጥነት የቀጥታ በረራ እናደርጋለን ሲሉም አስታውቀዋል።

mesfin.jpg
Mr Mesfin Tasew, Group Chief Executive Officer of Ethiopian Airlines. Credit: D.Kebede

አቶ መስፍን በመግለጫቸው እንዳሉት አየር መንገዱ የተለያዩ ስኬቶችን አስመዝግቧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት 4.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አክለው ገለጸዋል።

 ገቢው ከዕቅዱ የሁለት በመቶ፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው ያመላከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን፤ አየር መንገዱ ካገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 22 በመቶው ከዕቃ ጭነት (ካርጎ) የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 አየር መንገዱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 10.64 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገዱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 451 ሺህ ቶን ጭነት ማጓጓዙን አመልክተዋል።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን ከ145 በላይ እንዲሁም የሀገር ውስጦቹን 23 እንዳደረሰም ተናግረዋል።

EAL.jpg
Credit: D.Kebede

በአየር መንገዱ የስድስት ወራት ሪፖርት መሠረት ሰባት አዳዲስ አውሮፕላኖች ወደ ሥራ ተሠማርተዋል፤ አንድ ኤ350-1000 ኤርባስ፣ ሁለት ኤ350-900፣ አንድ ቦይንግ 787-800፣ ሶስት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለበረራ ውለዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጠቀምባቸው አውሮፕላኖች 147 ደርሰዋል።

በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በኢትዮጵያውያንና በሌሎች ሀገራት ላይ በጣለው የጉዞ እገዳ ምክንያት ወደ አሜሪካ ከተሞች የሚጓዙ መንገደኞች ቁጥር በመቀነሱ የአየር መንገዱ ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።

 አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ75 ሀገራት ዜጎች የፍልሰት ቪዛ (immigrant visa) መስጠት እንደምታቆም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለፈው ጥር ወር አስታውቋል።

ውሳኔው የሚመለከታቸውም፤ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ “ተቀባይነት በሌለው መጠን” ከመንግስት ድጎማ የሚቀበሉ ሀገራት ዜጎችን እንደሆነ መሥሪያ ቤቱ በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ከ4 የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በአጋርነት እየሠራ እንደሚገኝ ያመላከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ የነገሌ፣ የጎሬመቱ እና የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ተጠናቀው ሚያዝያ ወር ላይ ይመረቃሉ ብለዋል።

(ደመቀ ከበደ - ከአዲስ አበባ )


Share

2 min read

Published

Updated

By Demeke Kebede

Source: SBS


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now