ምዕመኑ በዓሉን ስለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በመፀለይና በማሰብ እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት የምግብ፣ የልብስና የመጠለያ እጥረት ያጋጠማቸው ወገኖቻችንን በመደገፍና በመርዳት ማክበር እንደሚገባው አሳስበዋል።
"ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ፍጹም ሰላም መስፈን ከልብ በመነሣሣት በዓሉን እናክብር" ሲሉም አባታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርነ ኢየሱስ ባስተላለፉት መልዕክት "የልደት በዓል የምስራች የሁሉም መሠረት የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱ እና በኛም መካከል ማደሩ ነው" ብለዋል።
"የልደት በዓልን ስናከብር ስለሰው ልጆች ክብር የምንሠራበት፣ ሕዝብ የሚከባበርበት፣ የሚዋደድበትና የሚተሳሰብበት ሊሆን ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ስለራቁት በመፀለይ፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለሕሙማን፣ በየጎዳናው ላሉ ወገኖች ያለንን በመስጠትና በማካፈል በዓሉን ማክበር እንደሚገባም የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ለኢየሱስ ክርስቶስ የገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የካውንስሉ ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ በዓሉን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ በኢትዮጵያና በተለያዩ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል የደስታና የፍቅር እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነትና ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም የወንጌል አማኞች በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የተሰጣቸውን ፍቅር ለሌሎች ማካፈል እንዳላባቸው አሳስበዋል።
ልዩነቶችን በዕርቅ በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እንትጋ ያሉት ቄስ ጀምበሩ÷ በተለይም የወንጌል አማኞች ፍቅርንና ሰላምን ከማወጅ ውጭ ሌላ መለኮታዊ ተልዕኮ የለንም ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚታዩ የልማት ሥራዎች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለጋራ ጥቅም መሥራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት መውጣት የሚቻል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም "የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን ስናከብር ለሌላቸው ወገኖች በማካፈል ሊሆን ይገባል" አስገንዝበዋል።
Share

