የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች የትግራይ ክፍለ አገር አዋሳኝ በሆኑት የአማራና አፋር ክፍለ አገራት የደህንነት ጥበቃ ያለው የእርዳታ አቅርቦትና የሠራተኞች ስምሪት ለማካሄድ የሚያስችል ስምምነት በተመድና የኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል መደረሱን ከኒው ዮርክ የመንግሥታቱ ጽሕፈት ቤት አስታውቀዋል።
ባለፈው ወር በፌዴራልና የትግራይ ክፍለ አገር ኃይላት መካከል በተካሄደው ግጭት በስድስት ሚሊየን ነዋሪዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩም ተገልጧል።
ተመድ በመግለጫው በሺህዎች የሚቆጠሩትን ለመፈናቀልና ሲልም ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን እንዲሰደዱ አስባብ በሆነው ግጭት ዞን እስካሁን ድረስ አቅርቦቶችን ማድረስ እንዳልተቻለ ገልጧል።
ናይሮቢ የሚገኘው የተመድ ሰብዓዊ ረድኤት ማስተባባሪያ ቢሮ ቃል አቀባይ ሳቪያኖ አብረዩ የመጀመሪያ ተልዕኮ የሚሆነው የአስፈላጊ አቅርቦቶች ግምገማ ከትናንት ረቡዕ እንደሚጀምር ተናግረዋል።
አክለውም ተመድ "ከሁሉም የግጭቱ ተሳታፊዎች" ጋር እንደሚገናኝና የእርዳታ ክፍፍሉም የሚካሄደው "አስፈላጊነቱን መሠረት ባደረገ ጥብቅ" ሁኔታ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በሌላም በኩል አቶ ዱጃሪች ከትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች በአማራና አፋር ክፍለ አገራት እንደሚገኙና ተመድ ያሉበትን ሁኔታ የመገምገም ዓላማ እንዳለው አስታውቀዋል።
የተመድ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሰኞ ዕለት ትግራይ ስደተኛ ካምፖች የሚገኙ 96,000 ኤርትራውያን ስደተኞችን ለመጎብኘትና እገዛም ለማድረግ ይቻለው ዘንድ ለኢትዮጵያ መንግሥት አቤቱታት አቅርቧል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ባባር ባሎሽ ከጄኔቫ "የረሃብና ተመጣጣኝ ምግብ አጥረት እውነተኛ አደጋ" የመሆኑ ስጋት በየሰዓቱ እየጨመረ እንደሚገኝ አሳስበዋል።
ተመድ በአሁኑ ወቅት በትግራይና አካባቢዋ ሁለት ሚሊየን ያህል እርዳታ የሚሹ እንዳሉና 45,000 ኢትዮጵያውያን ከትግራይ የሱዳንን ድንበር መሻገራቸውን ገልጧል።

