በምርጫው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የታዩ ክፍተቶች በተገቢው የሕግና የአሠራር ማሻሻያ እንዲታረሙ ኢሰመኮ ጠየቀ

*** የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

ኢሰመኮ ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2013 ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የክትትል ቡድን በማሰማራት ያጠናቀረውን የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ክትትሉ በተከናወነባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችና አካባቢዎች የተመለከታቸው ክፍተቶች ተገቢው ትኩረት እንዲያገኙና አስፈላጊውን የሕግና የአተገባበር መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል።

ኮሚሽኑ ለሀገራዊው ምርጫ 2013 ባለ6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ በማድረግና ለሰብአዊ መብቶች ትኩረት እንዲሰጥ ከመወትወት በተጨማሪ፤ በቅድመ ምርጫውና በምርጫው ቀን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሲያከናውን መቆየቱን የገለፀ ሲሆን  በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን በተመለከተና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ እንዲሁም ምርጫው የአካል ጉዳተኞችን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ያሳተፈና ለእነሱ ተደራሽ የሆነ በማድረግ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መከታተሉን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ 94 ባለሞያዎችን ያካተተ ቡድን በአጠቃላይ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ ከተሞችና በሁሉም ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች በሚገኙ 99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ፣ የአካባቢውን አስተዳደር፣ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን፣ እጩዎችንና አባላት እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ አካላትና ሌሎች ባለድርሻዎችን አነጋግሯል።

በዋና ጽሕፈት ቤቱ በተመደቡ ባለሙያዎች አማካኝነትም በስልክ ጥቆማዎችንና አቤቱታዎችን ተቀብሎ እንዳስተናገደ ገልጿል።

"ምርጫው የተካሄደበት አውድ በሀገር ውስጥ የተደራረቡ ችግሮች የገጠሙበት እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ባሉበት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምርጫው እንዲተላለፍ አስገዳጅ በሆነበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ምክንያት በእስር በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የማይዘነጋ መሆኑንና ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ" ኮሚሽኑ ገልጿል።

ይህ ተግዳሮት እንዳለ ሆኖ፤ ኢሰመኮ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው እለት ክትትል ባደረገባቸው  አካባቢዎች "የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት የታየ ቢሆንም፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች  የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየ" ገልጿል። ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የምርጫው ዕለት ሂደት ያለጎላ ችግር በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀና በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር አሳውቋል።

ኮሚሽኑ በምርጫው ሂደት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለተሳተፉና አስተዋጾ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ እውቅና ሰጥቶ፤ በቀሪው ሂደትም በሕጋዊና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል። 

ይሁንና እነዚህ አወንታዊና አበረታች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ከምርጫው እለት ጥቂት ቀናት በፊት፣ በምርጫው እለትና ከምርጫው ቀን በኋላ የደረሰ የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት፣ ተገቢ ያልሆነ እስር፣ በመራጮች ላይ የደረሰ ማስፈራራት፣ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ ስለደረሰ መጉላላትና ማዋከብ፣ የምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኛ ሰዎች ያለው ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተሳትፎ መጠን በሚመለከት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አስረድቶ፤ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ጥፋተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ እና ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠውን በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያግዱ፣ የሚገድቡ ወይም የሚያሰናክሉ ሁኔታዎች በተለይም የምርጫ ጣቢዎችን ያለ እንቅፋት የመጎብኘት አስፈላጊነት እና የእስር ቦታዎችን ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የመጎብኘት አስፈላጊነት በሚመለከት ለወደፊቱ ማናቸውም አይነት እንቅፋት እንዳይከሰት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካሎች ሁሉ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱና ሁሉም ሰዎችና ተቋሞች ለኮሚሽኑ ስራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ለ SBS በላከው መግለጫ አሳስቧል።

[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]


Share

Published

By Demeke Kebede

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
በምርጫው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የታዩ ክፍተቶች በተገቢው የሕግና የአሠራር ማሻሻያ እንዲታረሙ ኢሰመኮ ጠየቀ | SBS Amharic