"በጋምቤላ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል" - ኢሰመኮ

*** የክልሉ ኃላፊዎች በተለይም የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ የመንግስት ሠራተኞች ላይ ሲሰበሰብ የነበረው የፓርቲ አባልነት ክፍያን በተመለከተ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንደተወሰደ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገልጸዋል።

EHRC

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Commission. Source: Daniel Bekele

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አፋጣኝ ትኩረት እንደሚሻ አስታወቀ

የእስረኞችን አያያዝ ማሻሻል እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት ማረጋገጥ ይገባል ብሏል ኮሚሽኑ ለ SBS አማርኛ በላከው  መግለጫ፡፡

 በጋምቤላ ክልል ያለው የእስረኞች አያያዝና የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት በቂ ማሻሻያዎች ያሻል፤ እንደ መግለጫው።

ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 12 እስከ ታኅሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በጋምቤላ ከተማ እና በአኝዋክ ዞን በመገኘት በአካባቢው ስላለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ክትትል አድርጎ ከሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች ጋር መወያየቱን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የክልሉ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች አያያዝና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በተለይም በኦነግ ሸኔ አባልነት ተጠርጥረው በጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት ከታኅሣሥ ወር መግቢያ ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሁለት የ 11 እና የ 12 ዓመት ሕፃናት ወንዶች፣ እንዲሁም አንድ የ14 ዓመት ሕፃን ሴት በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ አሳስቦ፣ በተጠርጣሪዎች ሕፃናት ወንዶች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ያደረሱ የፀጥታ አባላት ላይ አፋጣኝ ምርመራ በማካሄድ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።

በተጨማሪም “ሕወሓትን በገንዘብ እና በተለያየ መንገድ ይረዳሉ፣ በክልሉ ውስጥ በሕዝብ መካከል ግጭት የመቀስቀስ ዓላማ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ምክንያት ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ 90 ተጠርጣሪዎች ላይ በፌዴራል ፖሊስም ሆነ በክልሉ ፖሊስ በኩል የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ሂደት አለመኖሩ በመገለጹ፣ ኮሚሽኑ ይህንኑ አሳሳቢ ጉዳይ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች አሳውቆ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በአፋጣኝ ምርመራ እንዲጀመርና የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ አሳስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው።

በሌላ በኩል፣ ኮሚሽኑ በጉብኝቱ ወቅት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ማነጋገሩን አሳውቋል።

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች ‘የምርጫ ሥነ ምግባር መግባቢያ ሰነድ’ የፈረሙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቢሮና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለማግኘት፣ በክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለመስራትና፣ የፓርቲያቸውን ዝግጅቶችን ለማድረግ እንግልት እንደሚገጥማቸውና በአንዳንድ አባላቶቻቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ መድረሱን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በእነዚህና ሌሎችም የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በተወያየበት ወቅት የክልሉ ኃላፊዎች ለሰብአዊ መብቶች መሻሻል በጎ ምላሽ ሰጥተው በተለይም የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ሲሰበሰብ የነበረው የፓርቲ አባልነት ክፍያን በተመለከተ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።

 

 

[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]

 


2 min read

Published

Updated

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now