"መንግሥት የሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም" - ኢሰመጉ

*** ኢሰመጉ፤ መንግሥት አሁን ላይ ችግሮቹን ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ ሕጋዊ፣ ትክክለኛ እና ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡

EHRC

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Commission Source: PD

ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀቻቸውና የሕጎቿ አካል ያደረገቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የሰብዓዊ  መብቶች ስምምነቶች እንዲሁም የሐገሪቱ የሕጎች ኁሉ የበላይ የሆነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥትም  ማንኛውም ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ የማይደፈርና የማይገሰስ ደህንነቱ በተጠበቀ ሰላማዊ ቦታ በህይወት  የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት እንዳለው ይደነግጋሉ፡፡

መንግሥት ደግሞ እነዚህን መብቶች  የማክበር እና የማስከበር ሕጋዊ እና ተፈጥሯዊ ግዴታዎች የመወጣት ቀዳማዊ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ ዲላ ጎጎላ ቃንቃ  ቀበሌ ላይ ታጣቂዎች በንጹኃን ሰዎች ላይ ባደረሱት ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት በርካታ ሰዎች  መሞታቸውን፣ መቁሰላቸውን እና የንብረት ውድመት መድረሱን ኢሰመጉ ከቦታው ከሚገኙ ተጎጂዎች  ለማወቅ ችሏል፡፡

ተጎጂዎቹ ጥቃቱ የተፈጸመው ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ በሚል የተጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም፣ አካባቢው ላለፉት በርካታ ጊዜያት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት እዝ ስር የነበረ መሆኑን ጠቅሰው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሠራዊቱ  አካባቢውን ለቅቆ ከወጣ በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ድርጊት ተጎጂዎች የደህንነት ስጋት እያለባቸው  ጥበቃ ሳይደረግላቸው ለዚህ ጉዳት የተዳረጉበትን ምክንያት ኢሰመጉ ለማጣራት ጥረት እያደረገ ነው፡፡

ከቀናት በፊት ኢሰመጉ የመንግሥትን ግዴታዎች ጠቅሶ ወቅታዊው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች  ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን እና አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ እንደሆነ ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

ኢሰመጉ  ላለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት፣ በተለይም ላለፉት ሦስት ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲከሰቱ ከነበሩ  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ትምህርት በመውሰድ መንግሥት ፈጣን እና መሠረታዊ የሚባሉ እርምጃዎችን  እንዲወስድ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ሆኖም፣ መንግሥት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ የመጣውን ዓይነተ-ብዙ  የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በአጭርም ሆነ በረዥም ጊዜ እርምጃ መፍታት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ይልቅ ሰበብ በመፍጠር ማለፍ ቀጥሎበታል፡፡

ማሳሰቢያ፡

ኢሰመጉ፤ መንግሥት አሁን ላይ ችግሮቹን ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድ ሕጋዊ፣ ትክክለኛ  እና ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡ በመሆኑም፤ ጉዳቱን በማድረስ እና በመደገፍ ለተፈጠሩት ችግሮቹ ኁሉ ተጠያቂ ናቸው በማለት የሚወንጅላቸውን አካላት በመግለጫዎች ከማውገዝ ባለፈ፣ በሕግ የተሰጠውን  ስልጣን ተጠቅሞ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እና ለተጎጂዎች ፍትሕ እንዲሰጥ ዳግም ይጠይቃል፡፡

መንግሥት በጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎች አፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ፣ በስጋት መኖሪያቸውን ለቅቀው የተፈናቀሉሰዎችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እና ንብረታቸው የወደመባቸውም ተመልሰው የሚቋቋሙበትን  መንገድ እንዲያመቻች ይጠይቃል፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ መንግሥት ተጨባጭ የደህንነት ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት የአጭር  እና የረዥም ጊዜ እቅዶችን በማዘጋጀት ወደ ፈጣን እርምጃ እንዲገባ፣ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ የሰብዓዊ  መብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸውን ቦታዎች ወደ ቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው በአፋጣኝ እንዲመልስ እና  በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጠሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ወደ ሥራ  እንዲያስገባ ኢሰመጉ ይጠይቃል፡፡

ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣

ኢትዮጵያ


2 min read

Published

Updated


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now