በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ መገደላቸው በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ኢሰመኮ የጥቃቱን ሂደት በተመለከተ ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት እና ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር ሲከታተልና ሲያጣራ መቆየቱን ገልጧል።
በማጣራት ሂደቱም ከቡለን ከተማ 90 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘው በኩጂ ቀበሌ የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች የሚኖሩባት ሲሆን ለቀበሌው የተመደበ የፖሊስ ወይም የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን እንደተረዳ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ባካሄደው ማጣራት ከዓይን እማኞችና የምልከታ ማረጋገጫ ስለደረሰባቸው ክስተቶች ሲገልጥ፤
- በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታ የተደረገላቸው ሲሆን አብዛኞዎቹ በጥይት ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን በምልከታ አረጋግጧል
- ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ደርሰውታል
- በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል። ቢያንስ 18 ያክል ነዶዎች ሲቃጠሉ ማየታቸውን አንድ ተጎጂ አስረድተዋል።
- በጨላንቆ እና ዶሼ ቀበሌዎች ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ከአካባቢው ለኮሚሽኑ የተላኩ መረጃዎች አመልክተዋል
- በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነ ተረድቷል።
- አካባቢውን በቅርበት እንዲጠብቅ የተመደበው ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማረጋጋት ተግባር ወደቦታው ተልከው የነበሩ አንድ የፌዴራል እና ሁለት የክልሉ አመራሮችን ለማጀብ በሚል አካባቢውን ለቅቆ መሄዱን አውቋል
- ጥቃቱ የጀመረው ይህንኑ ተከትሎ እንደሆነና ሌሊቱን የጀመረው ጥቃት እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ መዝለቁንም ለማወቅ ችሏል
- ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛው የሺናሻ ተወላጆች ናቸው። ከዚህ ቀደም በነበሩ ጥቃቶች ፈጻሚዎቹ ከ”ጫካ” የሚመጡ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በዚህኛው ጥቃት “በስምና በመልክ የሚያውቋቸው” የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸውለታል።
ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተደጋጋሚነትና የክልሉን ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ አስመልክቶ፣ የፌዴራሉንና የክልሉን መንግሥታት የተጠናከረ ትብብርና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ሲያሳስብ መቆየቱ ጠቁሞ፤ ከቶውንም “ጥቃቶቹ በመልክ እና በስፋት እየተባባሱ መጥተዋል” ስለሆነም “በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ሰዎች የህክምናና ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረብ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመር” ሲል አሳስቧል።
አያይዞም “በአካባቢው የሚገኘውን የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከር ኢሰመኮ ጥሪ ያቀርባል” ብሏል።

