የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ትናንት ምሽት ኦክቶበር 13 " አሳሳቢነቱ የቀጠለው የአገራችን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ " በሚል አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ብሔር ተኮር ጥቃት በተደጋጋሚ እየተፈጸመ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ- ኢሰመጉ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት፤ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በትኩረት እየተከታተለ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲገቱ እና የጥቃት ሰለባዎች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያሳስቡ መግለጫዎችን በማዘጋጀት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ሲወተውት መቆየቱን ገልጿል።
በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ የነፃነት እንዲሁም የንብረት መብት ሁኔታዎችን በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ፤ ሀሮ፣ ባጊን እና ኪረሙ ቀበሌዎች ከመስከረም ወር 2014 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በሸኔ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ይፈፀም እንደነበር፣ መስከረም 26/2014 በአካባቢው የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በግዳጅ ምክንያት ከአካባቢው በመሄዱ፤ ከመስከረም 30/2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት የሸኔ ታጣቂዎች በሀሮ ቀበሌ ተኩስ በመክፈት የአማራ ብሔር ሰዎችን እንደገደሉ፣ የአካል ጉዳት እንዳደረሱ እና ንብረት እንዳወደሙ መረጃዎች ለኢሰመጉ እንደደረሱትም አስታውቋል፡፡
ይህ መግለጫ አስከወጣበት ቀን ድረስ ታጣቂዎቹ በአካባቢው በመኖራቸው የሟቾችን አስክሬን ለማንሳት እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ህክምና ለመውሰድ አለመቻሉን፣ ሴቶች እና ሕፃናት አሁንም በጫካ ውስጥ እንዳሉ እና ለጥቃት እንደተጋለጡ እንዲሁም ነዋሪዎች በምግብ እጦት ላይ መሆናቸውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡
በተጨማሪም ለግዳጅ ሄዶ የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በ2/2014 ወደ ሀሮ ቀበሌ ተመልሶ የነበረ ቢሆንም አመሻሹን ተመልሶ መውጣቱን፣ በዚህም የሸኔ ታጣቂዎች በአካባቢው በብዛት እንዳሉ እና ነዋሪዎች በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን እንዲሁም ይህ መግለጫ እስከሚወጣበት ቀን ድረስ በአካባቢው የተኩስ ድምፅ እንደነበረ ለኢሰመጉ የሚደርሱት መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል፡፡

