ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ባለሙያዎች ማኅበር ነሐሴ 25 - 2012 ባወጣው መግለጫ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ዘብጥያ ወርደው ያሉ የአስራት ቴሊቪዥንና የኦሮሚያ ኔትዎርክ ጋዜጠኞች ሁኔታ ያሳሰበው መሆኑንና የብዙኃን መገናኛ ነፃነትም ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ጥሪ አቅርቧል።
ማኅበሩ በመግለጫው "ባለሙያዎቹ የተያዙበት ሁኔታ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሚያጋልጥ ሁኔታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ቤተሰብን ጨምሮ በተለያዩ አካላት የመጎብኘት መብታቸው ችግር ውስጥ እንዳለ ተረድተናል" በማለት መንግሥት ለባለሙያዎቹ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ ፍትሕ እንዲያገኙ አሳስቧል።
አያይዞም፤ በቅርቡ በዎላይታ የዎጌታ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ በጸጥታ ኃይላት ተዘፍቶ መልሶ የመከፈቱን ሁኔታ አንስቶ እንዲያ ያለው ተፅዕኖ በየትኛውም የሚዲያ ተቋም ላይ እንዳይደገም አመላክቷል።
በታካይነትም ለመንግሥት ባቀረበው ማሳሰቢያ "ተስፋ የተጣለበት የመገናኛ ብዙኅን ነፃነትን የማክበር ምሕዳር ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲያድግ [መንግሥት] የበኩሉን እንዲወጣ ማሳሰብ እንወዳለን" ብሏል።

