ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት፣ በተለይም በአሰኮ፣ በሽርካ፣ በሆንቆሎ፣ በዋቤና በሙኔሳ ወረዳዎች በቤተ ክርስቲያናትና በምእመናን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት ማስከተላቸውን ገልጸዋል።
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የጠላታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በእሳት መቃጠሉ ተገልጿል።
በተጨማሪም የካራ ኩፍቴና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን መዘረፉንና የቤተ ክርስቲያኑ ንብረቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን መግለጫው አመልክቷል።
መግለጫው አክሎም በርካታ ምእመናን በግፍ መገደላቸውን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል። በአካባቢው የተፈጠረው ሁኔታ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት እና የደኅንነት ችግር መፍጠሩም ተጠቁሟል።
አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅና ሰላምን የማስፈን ሕጋዊ እና ሞራላዊ ኃላፊነት የተጣለባቸው የጸጥታ አካላት በቤተ ክርስቲያናትና በምእመናን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አሳስበዋል። እንዲሁም በጥቃቶቹ ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ተገቢውን የሕግ ተጠያቂነት እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ምዕመናንና መላው ኢትዮጵያውያን በጥቃቶቹ ሳቢያ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በሰብአዊ ድጋፍ፣ በአጋርነት እና በማጽናናት እንዲያግዙ፣ የሀገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር፣ ዜጎችም ከጥቃትና ከመፈናቀል እንዲጠበቁ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

