በጅሮንድ ጆሽ ፍራይደንበርግ ፌስቡክ አውስትራሊያ ላይ ጥሎ የነበረውን ዕገዳ በማንሳት በመጪዎቹ ቀናት የአውስትራሊያ ዜና ገጾች መልሶ በማኅበራዊ ገጹ ላይ እንደሚያኖር ማስታወቁን ገለጡ።
ባለፈው ሳምንት በፌዴራል መንግሥቱና ፌስቡክ መካከል ለአውስትራሊያ ዜናዎች ክፍያ እንዲፈጸም ግድ በሚለው የሚዲያ ረቂቅ ድንጋጌ ሳቢያ በተፈጠረው ፍጥጫ ፌስቡክ የመላ አውስትራሊያ የዜና አውታሮች ላይ ዕገዳ ጥሎ ነበር።
ሆኖም አቶ ፍራይደንበርግ በዛሬው ዕለት ማክሰኞ ፌብሪዋሪ 23 እንደገለጡት ከፌስቡክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከበርግ ጋር ባደረጉት ንግገር መሠረት መንግሥት በረቂቅ ድንጋጌዎቹ ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግና በአጸፋውም ፌስቡክ የአውስትራሊያ ዜና ስርጭቶች ላይ ጥሎ የነበረውን ዕገዳ እንደሚያነሳ ከስምምነት ላይ መደረሱን ሲያስረዱ፤
" ባለፉት ቀናት ላካሄድናቸው ገንቢ ባሕርይ ለተላበሱ ውይይቶች ማርክ ዙከበርግን ላመሰኝ እወዳለሁ። ሂደቶቹ አዋኪ የነበሩ ቢሆኑም በጣሙን ጠቃሚ ጉዳዮች ናቸው" ብለዋል።
***
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን መንግሥታቸው በክሬይግ ኬሊ ከሊብራል ፓርቲ መሰናበት አቅጣጫውን አይስትም አሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ከሊብራል ፓርቲ ስንብት ማለት የፌዴራል መንግሥቱ በምክር ቤት ያለው አብላጫ ድምፅ በአንዲት ወንበር ብቻ እንዲወሰን ያደርጋል።
አቶ ክሬይግ የኮሮናቫይረስን አስመልክቶ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት በብርቱ እየተወገዙ ያሉ ሲሆን፤ ስኮት ሞሪሰን የፓርቲ ስንበት ወረቀታቸውን መቀበላቸውን አስታውቀዋል።
ሆኖም አቶ ክሬግ ምንም አንኳ ከሊብራል ፓርቲ ቢሰናበቱም ለመንግሥት ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

