ከዛሬ ነሐሴ 1 - 2012 ተጀምሮ እስከ ነሐሴ እኩሌታ የሚዘልቀውን ጾመ ፍልሰታ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ ሃይማኖታዊ መልዕክትና አገራዊ ማሳሰቢያዎችን አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኩል - አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ የዘንድሮው ጾም የሚከናወነው በአገረ ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ተከስቶ ባለበት ሁነት መሆኑን አመላክተዋል።
ከእነዚህ ክስተቶች ለትድግና ለመብቃትም በንጹህ ልቦና ንስሃ መግባትና ፈሪሃ እግዚአብሔርን ማሳደር እንደሚገባ ሲያስገነዘቡ፤
“እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በምንሰራው ሥራ፤ በምንናገረው ቃል፤ በምናስበው ሀሳብና ምኞት ሁሉ እግዚአብሔር ያውቅብናል፣ ይፈርድብናል፣ ያየናል የሚል አስተሳሰብ በውስጣችን አድሮ ከክፉ ድርጊት መቆጠብ ነው” ሲሉ ምዕመናን አፍ ተልብ እንዲሆኑ ክርስቲያናዊ ቃለ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ጾመ ሳምንታቱን ከአገራዊ ጉዳዮች ጋር አያይዘውም “ኢትዮጵያ የዚህ ትውልድ ብቻ ሳትሆን ያለፈውም የወደፊቱም ጭምር ናት” በማለት ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን በውይይት እንዲፈቱ፣ ይቅርታና ዕርቅን እንዲተገብሩና በአንድነት የቆመች አገርን ለቀጣዩ ትውልድ የማሳለፍ የዜግነት ግዴታን ተገንዝቦ መወጣት ግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።
አገራዊ ሰላም፣ አንድነትና ልማት እንዲሰፍንም አባታዊ ተማፅኖ አቅርበዋል።
በተለይም ኮሮናቫይረስ ተክስቶ ባለበት የጾመ ፍልሰታ ወቅት የኦቶዶክስ እምነት ተከታዮች ችግረኞችን እንዲታደጉ የረድኤት ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኩል ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ 'የእንኳን ለጾመ ፍልሰታ አደረሳችሁ' መልዕክታቸውን ለካቶሊክ እምነት ተከታዮች አስተላልፈዋል።
ምዕመናኑ ተከስቶ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የጥንቃቄ መርሆዎችን እየተገበሩ ጾምና ጸሎታቸውን እንዲፈጽሙ፤ የዘርና የጾታ ልዩነቶችን በማስወገድ በፍጹም ትህትና ችግረኞችን እንዲታደጉና ሰላምና መከባበር እንዳይለያቸው አሳስበዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ - አገራዊ ጉዳዮችንም አንስተው ፖለቲከኞች አገርን ለመምራት የሚችሉት 'በሕዝብ ልብ በመንገስ እንጂ፤ ኃይልን፣ ሁከትንና በደልን መሳሪያ በማድረግ' እንዳልሆነ ልብ አሰኝተዋል።
በጾመ ፍልሰታው ምዕመናን 'ዘረኝነትና ጥላቻን በኢትዮጵያዊ አብሮነት' ተክተው በፍቅር እንዲጸልዩ የመንፈሳዊ መሪ ምክራቸውን ለግሰዋል።

