እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እና አሜሪካ (USA) አንድ ክፍለ-ዘመንን የተሻገረ እና በጠንካራ መሠረት የተገነባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሁለት ሉዓላዊ ሀገራት ናቸው፡፡ ግንኙነታቸው በመንግስታት ደረጃ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በሕዝብ ለሕዝብ ጭምር የተደገፈ ከመሆኑም ባሻገር፤ በትምህርት፣ በጤና፣ በምጣኔ-ሀብት እና በሌሎችም በርካታ የትብብር መስኮች አብረው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለሁለቱ ሉዓላዊ ሀገራት የሰመረ ግንኙነት ዕውቅና ሰጥቶ፤ ግንኙነታቸው እየጎለበተ እንዲሄድ የበኩሉን ድርሻ ሁሉ ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ይህንንም ተግባሩን በቁርጠኝነት አጠናክሮ የሚቀጥልበትም ይሆናል፡፡
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች
የተለያዩ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለዛሬ ጠንካራ ደረጃ የደረሰው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ይበልጥ እየዳበረ እንዲሄድ ሁለቱም ሀገራት የበኩላቸውን በጎ የትብብር ሥራዎች በሚያከናውኑበት በዚህ ወቅት ታዲያ፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስቲያ በነጩ ቤተ-መንግስታቸው ሆነው፤ ጎረቤታችን ግብጽ ታላቁን የኀዳሴ ግድባችንን እንድታፈነዳው እና እንድትደረምሰው ትዕዛዝ መሰል ምክረ-ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
ይህንን ፍላጎታቸውንም በማያሻም አኳኋን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ እጅጉን ኃላፊነት በጎደለው እና ከአንድ የሀገርን ከፍተኛ ስልጣን ከያዘ መሪ በማይጠበቅ ንግግራቸውም፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጅጉን አዝኗል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም-አቀፍ ሕግጋት መሠረት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና የውኃ አካላት የጋራ ሀብት መሆናቸውን በማመን፤ ከግድቡ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ሁሉ በግልጽ እና በሕጋዊ ድርድሮች ብቻ እንዲፈቱ ስትጥር መቆየቷ ይታወቃል፡፡
ፓርላማችንም ለዚሁ የጋራ ብልጽግና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ የሚጠበቅበትን ሲያከናውን እንደቆየው ሁሉ፤ ከታችኛዎቹ የአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮች እንዲቀጥሉ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ይሁን እንጂ በማስፈራራት እና በዛቻ የሚቀየር ወይም ተጠቃሚ የሚሆን ወገን ስለማይኖር ፕሬዚዳንቱ ይህንን ፈር የሳተ ንግግራቸውን እንዲያርሙ እየጠየቅን፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግን ከማናቸውም ጊዜ በበለጠ ለሀገራቸው ክብር፣ ጥቅም፣ ሉዓላዊነት እና ብልጽግና በጋራ እንዲቆሙ ምክር ቤቱ ይጠይቃል፡፡
ግድባችን የሉዓላዊነታችን እና የብልጽግናችን ማኅተብ ነው! ኢትዮጵያ በልጆቿ መሥዋዕትነት ታፍራ እና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር…!!!

