በአቶ ስብሃት ነጋ፣ በአቶ አባይ ወልዱና በወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ሶሰት መዝገቦች የተያዙ 20 የቀድሞ የሕወሃት አመራሮች ተጨማሪ የ14 ጊዜ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ።
ሃያ የቀድሞ የሕወሃት አመራሮች በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።
በአቶ ስብሃት ነጋ መዝገብ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ፣ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ፣ ወይዘሮ ምህረት ተክላይ፣ አቶ ወልደጊዮርጊስ ደስታና አቶ ገብረመድህን ተወልደ በድምሩ ዘጠኝ ግለሰቦች ቀርበዋል።
አቶ ስብሃት፣ ወይዘሮ ቅዱሳን፣ አቶ አባዲ፣ ወይዘሮ ምህረትና አቶ ቴዎድሮስ የተባሉት ተጠርጣሪዎች በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ በአቶ ሰዩም መስፍን ከሚመራ የህወሃት አመራር ጋር በመሆን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ ከተለያዩ ክልሎች ወጣቶችን መልምለዋል ተብሏል።
እንዲሁም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ሰነድ በማዘጋት የክልሉን ልዩ ሃይልና የከዱ የሰራዊት አባላትን በማደራጀትና ለጦርነት በማዘጋጀት ወንጀል መጠርጠራቸውን ፖሊስ አስረድቷል።
ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፣ አቶ ተክለወይኒ አሰፋና አቶ ገብረመድህን ተወልደ ደግሞ ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር በመሆን የጥቅምት 24ቱ ጥቃትና የጦር መሳሪያ ዘረፋ እንዲፈጸም አድርገዋል በሚል ተጠረጥረዋል።
ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ የተባሉት ተጠርጣሪ በክልሉ ለምሽግ ማስቆፈሪያ ማሽኖችን በማዘጋጀት ሲያስቆፍሩ እንደነበረና የነዳጅ ዴፖ በማስዘረፍ እንዲደበቅ በማድረግና ገንዘብና ሎጀስቲክስ በማቅረብ ወንጀል ስለመጠርጠራቸው ተወስቷል።
በሁለተኛው መዝገብ ደግሞ የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አባይ ወልዱን ጨምሮ ዶክተር አብርሃም ተከስተ፣ ዶክተር ረዳኢ በርሔ፣ አቶ ሙለታ ይርጋ፣ አቶ ኪሮስ ሃጎስ፣ አቶ እቁባይ በርሄ፣ አቶ ጌታቸው ተፈሪ፣ አቶ ንጋቱ አንገሶምና አቶ አምደማርያም ተሰማ በድምሩ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ቀርበዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በመጀመሪያው መዝገብ በተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት ማለትም የትግራይን ልዩ ሃይልና የከዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በማደራጀት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በማድረግና ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ ወንጀል መጠርጠራቸው ተገልጿል።
ከተርጣሪዎቹ መካከል ዶ/ር አብርሃም ተከስተ የአገሪቷን የወርቅ ሃብት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ትግራይ ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ በማዘዋወር፣ ነዳጅ እንዲዘረፍ በማድረግና በምሽግ ቁፋሮ ለተሰማሩ ሃይሎች እየተዘዋወሩ ገንዘብና ሎጂስቲክስ በማቅረብ ተጠርጥረዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲደርስ ካደረጉ በኋላ ራሳቸውን በመደበቅ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ለአብነትም አቶ አባይ ወልዱ ሀሰተኛ ሰም ያለበት መታወቂያ በመያዝ የቄስ ልብስ ለብሰው መያዛቸውን አስረድቷል።
በሶስተኛው መዝገብ የተካተቱት ወይዘሮ ኬሪያ ኤብራሂምና ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሄር ሲሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ከላይ በሁለቱ መዝገቦች በተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረዋል።
በሶስቱ የምርመራ መዝገቦች በመጀመሪያው የ15 ሰዎችን፣ በሁለተኛው መዝገብ የ10 ሰዎችን፣ በሶስተኛው መዝገብም የ10 ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን ፖሊስ አስረድቷል።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል በመሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ከሚመለከታቸው ተቋማት የጉዳት ዝርዝር መጠን እንዲላክለት ደብዳቤ መጻፉን ገልጿል።
ወንጀሉ ሰፊና ውስብሰብ በመሆኑ፣ ሌሎች የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብና የቴክኒክ ምርመራ ውጤት ለመቀበል ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ ምርምራ ሊያስተጓጉሉና ሰነድ ሊያጠፉ ስለሚችሉ የዋስትና መብታቸውን ተቃውሟል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ያቀረበው የወንጀል ድርጊት ጥቅል የወንጀል ተግባራት እንጂ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ተሳትፎ በዝርዝር አለመቅረቡንና ከዚህ በፊት ካቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ አመክንዮ የተለየ አላቀረበም በሚል ተከራክረዋል።
ተጠርጣሪዎቹም ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ያለ ፍርድ ቤቱ ፈቃድ ምስላቸው መቀረጽና በቴሌቪዥን መታየት ተገቢ አልነበረም፣ ሚዲያዎች ሲዘግቡም ሚዛናዊ መሆን አለባቸው በሚል አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡
አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች በዕድሜ የገፉና የጤና ችግርም ያለባቸው በመሆኑ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድም ጠይቀዋል።
ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በሚል ያቀረበውንና የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ችሎቱ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
ኢዜአ
ባልደራስ

