ከአፋር ዲፕሬሽን እስከ አንቀጽ 39

ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ አኅጉር ለሁለት የመሰነጠቅ 'ምጥ' ላይ ትገኛለች። ሆኖም ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት እጅግ አዝጋሚ ከመሆኑ የተነሳ፣ ፍጥነቱ ከሰው ልጅ የጥፍር ዕድገት አይበልጥም። በአንጻሩ ግን፣ በኢትዮጵያውያን መካከል እየታየ ያለው ፖለቲካዊ መሰነጣጠቅና የማንነት ውጥረት ፍጥነቱ የሚለካው በሰዓታትና በቀናት ልዩነት በሚፈነዱ ግጭቶች ነው። ታዲያ ከእነዚህ ሁለት ፈታኝ ክስተቶች መካከል፣ የትኛው ስንጥቅ ይሆን ቀዳሚውና አጣዳፊው የህልውና ሥጋታችን? በአለት ላይ የታተመው አዝጋሚ ሂደት ወይስ በልብ ውስጥ የሰረጸው ፈጣን ስብራት?

gettyimages-2247821497-612x612.jpg

An infographic titled "Ethiopian volcano erupts for first time in 12,000 years" was created in Ankara, Turkiye, on November 25, 2025. The Hayli Gubbi volcano, the southernmost in the Mount Erta Ale range in Ethiopia's northeastern Afar region, erupted for the first time in thousands of years. Credit: Anadolu/Anadolu via Getty Images

የአፋር ትሪያንግል፦ የሶአፋር ትሪያንግል፦ የሶስት ፕሌቶች (ምድረ ንጣፎች) መገነጣጠል

በአፋር ክልል የሚገኘው የሃይሊ ጉቢ እሳተ ገሞራ ተራራ ለአሥራ ሁለት ሺሕ ዓመታት በጥልቅ እንቅልፍ ቆይቶ ነበር። ሆኖም ህዳር 16 ቀን ድንገት ከዘመናት መኝታው በመንቃት፣ አካባቢውን በታላቅ ድምፅ፣ በጭስ፣ በአመድና በላቫ አናወጠው። የፍንዳታው ጭስ አምድ ልክ እንደ ተወንጫፊ ሮኬት እስከ 45,000 ጫማ (13 ኪሎ ሜትር) ከፍታ ድረስ መወርወሩን ሳተላይቶች መዝግበዋል።

ይህ አገር አቋራጭ ንፋስ የቀላቀለው አመድና ጭስ፣ ቀይ ባሕርን፣ ኦማንን እና የመንን ተሻግሮ እስከ ሕንድ ድረስ የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎችን አስተጓጉሏል።

ከፍተኛ ሙቀትና ርጥበት ያዘሉ የእሳተ ገሞራ ፍንጣቂዎች (Pyroclastic clouds) ባሉት ደመና ውስጥ አውሮፕላኖች አቋርጠው ሲያልፉ፣ አመዱ በአካላታቸው ላይ እንደ ሲሚንቶ ይለሰናል፤ ይህም ሞተሮች እንዳይሽከረከሩ በማድረግ በአየር ላይ ድንገተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።

ለዚህም እንደ አብነት በ2010 (እ.ኤ.አ.) የአይስላንድ እሳተ ገሞራ (Eyjafjallajökull) መፈንዳቱን ተከትሎ የተነሳውን ግዙፍ የአመድ ደመና መጥቀስ ይቻላል። በወቅቱ ደመናው መላውን አውሮፓ በማጥለቅለቁ በርካታ በረራዎች የተቋረጡ ሲሆን፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ወደ አውሮፓ ያደረጉትን ጉዞ ለማሳጠር ተገደው ነበር።

ይህ ክስተት እሳተ ገሞራዎች ከሚፈነዱበት ስፍራ በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ላይ እንኳ ሳይቀር፣ ምን ያህል ከፍተኛ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ማሳያ ነው።

እነዚህ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች የሚከሰቱት ሶስት የምድር ንጣፎች (Plates) በሚዋሰኑበት ቀጠና ነው። እነዚህም የኑቢያ (ወደ ሰሜን-ምዕራብ)፣ የአረቢያ (ወደ ሰሜን-ምስራቅ) እና የሶማሊያ (ወደ ደቡብ-ምስራቅ) ንጣፎች ሲሆኑ፣ ለበርካታ ሚሊዮን ዓመታት እርስ በእርስ በመወጣጠር ላይ ይገኛሉ።

ለዚህም ነው በአፋር አካባቢ የምድር ቅርፊት (Crust) እጅግ ከመሳሳቱ የተነሳ በተደጋጋሚ የሚሰነጠቀው፤ እንዲሁም ላቫ፣ ፍል ውሃና ተከታታይ የምድር ንዝረቶች በስፋት የሚታዩት።

የሦስትዮሽ መገናኛ (Afar Triple Junction) በመባል የሚታወቀው ይህ አካባቢ የሦስት ታላላቅ ስምጥ ሸለቆዎች የትኩረት ማዕከል ነው።

በእነዚህ ስምጦች ውስጥ በሂደት የሜዲትራኒያን እና የሕንድ ውቅያኖስ ውሃዎች ሰርገው በመግባት ቀይ ባሕርን እና የአደን ባሕረ ሰላጤን ፈጥረዋል። ሦስተኛው ስንጥቅ ደግሞ አሁንም ድረስ በሚሊዮን ዓመታት ሂደት አዲስ ባሕርን የማዋለድ አዝጋሚ 'ምጥ' ላይ የሚገኘው ታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ነው።

በፕሌት ቴክቶኒክስ ሳይንሳዊ ንድፈ-ሐሳብ መሠረት፣ ይህ ሂደት አፍሪካን ለሁለት እንደሚከፍላት ከታወቀ ግማሽ ክፍለ ዘመን አልፎታል። ጉዳዩ ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡም ሆነ ለመገናኛ ብዙኃን አዲስና እንግዳ ሊመስል ቢችልም፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ሙያተኞች ግን ለዘመናት የታወቀና 'ፀሐይ የሞቀው' እውነታ ነው።

ጂኦሎጂያዊ ሂደት እና የመረጃ መዛባት

የአኅጉራት መከፋፈል ጉዳይ ከሳይንሳዊ ትንታኔ ባሻገር ሃይማኖታዊ አንድምታም አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘፍጥረት 10፡25 ላይ የሚገኘውን 'ምድር በዘመኑ ተከፋፍላለችና' የሚለውን ሐረግ መሠረት በማድረግ፣ አህጉራት የተከፋፈሉት ከኖኅ የጥፋት ውሃ በኋላ እንደሆነ የሚጠቁሙ ወገኖች አሉ።

በአንጻሩ ዘመናዊ የሃይማኖት ሊቃውንት ይህንን ጥቅስ እንደ ሕዝቦች መበተንና መከፋፈል አድርገው ይተረጉሙታል። ቅዱስ ቁርኣን የአህጉራት እንቅስቃሴን በግልጽ ባይጠቅስም፣ አንዳንድ እስላማዊ ጸሐፊዎች ጉዳዩን በምዕራፍ 54 ቁጥር 1 ላይ ከተጠቀሰው የጨረቃ መከፈል (The Splitting of the Moon) ተአምር ጋር በምሳሌነት ያያይዙታል።

ሆኖም በምሥራቅ አፍሪካ ፕሌቶች እንቅስቃሴ ዙሪያ በመደበኛም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ በስህተትና በግነት የተሞሉ ናቸው።

በእርግጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን የጂኦሎጂ ምሁራን በዘርፉ ጥልቅ ምርምሮችን በማካሄድ፣ ውጤቶቻቸውን በዓለም አቀፍ መድረኮችና በታወቁ ሳይንሳዊ መጽሔቶች ላይ በማሳተም ከፍተኛ አካዳሚያዊ ዕውቅናን አትርፈዋል።

ይሁን እንጂ፣ ይህንን ውስብስብ ሳይንሳዊ ዕውቀት ለአገር ውስጥ አንባቢ በሚመጥን መልኩ አቅልሎና በአገራዊ ቋንቋዎች ተርጉሞ በማቅረብ ረገድ ሰፊ ክፍተት ይስተዋላል።

ምሁራኑን ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን የምናያቸው፣ አንድ አደጋ ከተከሰተ በኋላ ቀርበው የክስተቱን ሥፍራና የንዝረት መጠን ብቻ ሲገልጹ ነው። ይህ ደግሞ ሳይንሳዊ ዕውቀትን አስቀድሞ በማጋራት ሕዝብን የማንቃትና የተሳሳቱ መረጃዎችን የማረም ሙያዊ ኃላፊነታቸው ገና ብዙ መሥራት እንደሚቀረው ያሳያል።

በተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ሳቢያ፣ በተዛቡ አረዳዶች ላይ የተመሠረቱ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።

በአሁኑ ወቅት በአፋር አካባቢ ያለውን የምድር እንቅስቃሴ ለሕዝብ ለማስረዳትና 'ቅድመ-ማስጠንቀቂያ' ለመስጠት የሚሞክሩ፣ በርካታ ተከታዮች ያሏቸው ወገኖች ቁጥር ቀላል አይደለም። እንዲያውም ሕዝቡም ሆነ መንግሥት የጥንቃቄ ዝግጅቶችን ከወዲሁ እንዲጀምሩ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ሆኖም እነዚህ ወገኖች የሚያሰራጯቸው መረጃዎች ሳይንሳዊ እውነታን የሳቱ በመሆናቸው፣ በማኅበረሰቡ ላይ አላስፈላጊ ስጋት እንዳይፈጥሩ መሠረታዊ የሆኑ ማስተካከያዎችና የማንቂያ እርምጃዎች መወሰዳቸው ግድ ይላል።

በተለይም በሌሎች የባህላዊ ዕውቀት ዘርፎች ሰፊ ተቀባይነትና አድናቆት ያተረፉ ግለሰቦች፣ ይህን ያልተካኑበትን ጉዳይ ለተከታዮቻቸው ሲያብራሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፤ ምክንያቱም ትምህርቱንና ማስጠንቀቂያውን እየሰጡ ያሉት ዝና ባተረፉበት የዕውቀት መስክ ስላልሆነ ነው።

እርግጥ ነው፣ ስለ መሬት መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራ ከወላጆቻቸው የወረሱት ጥልቅ የባህላዊ ዕውቀት ቢኖራቸው፣ ወይም ቢያንስ በአፋር አካባቢ ለረጅም ዘመናት ኖረው ክስተቱን በቅርበት ቢታዘቡት ኖሮ፣ ትንታኔያቸው የተሻለ ተዓማኒነት በኖረው ነበር።

ሊሰመርበት የሚገባው መሠረታዊ ነጥብ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚወራው የአባይ ወንዝ፣ የጣና ሐይቅ፣ ደቡብ ሱዳን እና ካይሮ ከዚህ ጂኦሎጂያዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት አደጋ አይጋረጥባቸውም። እነዚህ አካባቢዎች አዲስ ከሚፈጠረው ስንጥቅና የባሕር ወለል ሥፍራ እጅግ ርቀው የሚገኙ በመሆናቸው፣ ከክስተቱ ጋር ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም።

በተያያዥነትም፣ "የደቡብ ሱዳን ፕሌት" ተብሎ የሚታወቅ ፅሁፍም ሆነ ካርታ የለም። በአካባቢው የሚገኙት ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሦስቱ ፕሌቶች (የኑቢያ፣ የአረቢያ እና የሶማሊያ ፕሌቶች) ብቻ መሆናቸውና አራተኛ ፕሌት እንደሌለ ግልጽ ሊሆን ይገባል።

እሳተ ገሞራ ሲፈጠር የሙቀት መጠኑ ከ 700°C - 1200°C ስለሚደርስ ማንኛውንም ነገር እንደ ውሃ መቅለጡ ግልፅ ነው።

በመሆኑም እንደ ባክቴሪያ ያሉ ረቂቅ ተሕዋስያንም ሆኑ ተቀብረው የነበሩ ጥንታዊ የሥልጣኔ ቅርሶች በዚህ ጽኑ ሙቀት ቀልጠው ከመጥፋት ውጭ፣ በእሳተ ገሞራ ላቫ ታጅበው ወደ ገጸ-ምድር ሊመጡ የሚችሉበት ምንም ዓይነት አመክንዮ አይኖርም። በእሳተ-ገሞራው ላቫ ውስጥ፣ የትናንት ትውስታ ሁሉ አመድ ሆኖ ይቀራልና

እንደው በባህላዊ ዕውቀት አራማጆች አብሮ ይመጣል የተባለው “መርዘኛ ባክቴሪያ” በተአምር በላቫው ከፍተኛ ሙቀት አይሞትም ብለን እንኳ ብናስብ፣ የእሳተ ገሞራ ላቫ ፍሰት በተፈጥሯዊ አጥርና በፊዚክስ ሕግጋት የሚገዛ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

ለዚህም የሚከተሉትን ሦስት መሠረታዊ ነጥቦች ልብ ማለት ይገባል፦

1. የሚፈሰው ላቫ በቀጥታ ቀይ ባሕርን የመቀላቀል ዕድል የለውም። በአፋር ትሪያንግል እና በቀይ ባሕር መካከል የሚገኘው የአፋር ብሎክ ማውንቴን (Danakil Horst) እንደ ተፈጥሯዊ ግድብ ሆኖ ስለሚጋርደው፣ ላቫው ወደ ባሕር እንዳይደርስ ይከለክለዋል።

2. የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ጠባይ የሚወሰነው በውስጡ ባለው የሲሊካ (SiO2) መጠን ነው። የሲሊካ መጠኑ ከፍተኛ ሲሆን ፍንዳታው ኃይለኛና ቁሳቁሶችን በቅጽበት ወደ ሰማይ የሚረጭ ይሆናል። በአንፃሩ የሲሊካ መጠኑ ዝቅተኛ በሚሆንበት ጊዜ፣ ላቫው እንደ ወራጅ ውሃ በዝግታ ወደ ቁልቁል የመፍሰስ ጠባይ ይኖረዋል።

3. ላቫ፣ እንደማንኛውም ፈሳሽ አካል፣ በፊዚክስ ሕግ የሚገዛ በመሆኑ ከከፍተኛ ሥፍራ ወደ ዝቅተኛ ሥፍራ እንጂ፣ ከዝቅተኛ ተነስቶ ወደ ከፍተኛ ቦታ የመፍሰስ ተፈጥሯዊ ዕድል የለውም። በመሆኑም የእሳተ ገሞራ ላቫ ከአፋር ዝቅተኛ ሥፍራዎች ተነስቶ፣ ከባሕር ወለል በላይ ከሁለት ሺሕ ሜትር በላይ ከፍታ ወደሚገኙት እንደ ጎጃም ያሉ ደጋማ ቦታዎችና ሸለቆዎች አሻቅቦ የሚፈስበት ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም የፈሳሽ ፍሰት ሁልጊዜም በስበት ኃይል (Gravity) ሕግ የሚመራ ነውና።

“የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ የሚኖረው ዕድሜ ከሚሊዮኖች ዓመታት የጂኦሎጂ ሂደት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት በመሆኑ፣ የአህጉሩ መከፈል ምን ያህል ሊያሰጋን ይችላል?” የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው።

በተለይም በሀገራችን አንጋፋ እናቶችና አባቶች ዘንድ የሚዘወተረው “ስምንተኛው ሺህ የዓለም ፍጻሜ ነው” የሚለው ትርክት አሁንም ድረስ በብዙዎች ልብ ውስጥ ይስተጋባል።

በእርግጥም፣ በዓለም ላይ የሚታዩት የሞራል ዝቅጠቶችና ተደጋጋሚ የተፈጥሮ መናወጦች የዓለም ማብቂያ ምልክቶች መሆናቸውን በርካታ ሃይማኖቶች ያስተምራሉ።

በሳይንሱም ቢሆን፣ የምድራችንን ሕልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እንደ አስትሮይድ ግጭት፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥና የኒውክሌር ጦርነት ያሉ ሥጋቶች በተደጋጋሚ ይጠቀሳሉ።

በሀገራችንም ቢሆን፣ “ኢትዮጵያ ከዛሬ ነገ ትፈርሳለች” ብለው አፍራሽ ትንቢት የሚናገሩ ወገኖች አሉ። በተቃራኒው ደግሞ የሰው ልጅ ቴክኖሎጂ ተመንድጎ ወደፊት የምድርን ፕሌት እንቅስቃሴ እንኳ ሳይቀር በቁጥጥር ሥር በማዋል ሕልውናውን ያረጋግጣል የሚል ብሩህ ተስፋ ያላቸውም አልጠፉም።

ከባሕር አልባነት ወደ ባሕር ኃያልነት

“አይሆንም”ን ትተን “ይሆናል” በሚል መነሻ፣ የምድራችንም ሆነ የአገራችን ፖለቲካዊ ካርታ እስከ አራት ሚሊዮን ዓመታት ድረስ አሁን ባለበት ቅርጽ ይቆያል ብለን ብንገምት፤ የስምጥ ሸለቆን ይዞታ፣ የአገራዊ መስተዳድሮች ድንበርንና የከተሞችን ስርጭት በጂኦግራፊያዊ የመረጃ ሥርዓት (GIS) አነባብረን ብናሰላቸው የሚከተሉትን አስገራሚ ለውጦች እናያለን።

በመጀመሪያ፣ 'የሶማሊያ ፕሌት' በመባል የሚታወቀውና ተገንጥሎ የሚሄደው አነስተኛው የአፍሪካ ፍንካች፤ ምሥራቃዊ የኢትዮጵያን ክፍል፣ መላው ሶማሊያን እንዲሁም የምሥራቅ ኬንያን፣ የታንዛኒያንና የሞዛምቢክን ግዛቶች ይዞ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ ይጓዛል።

በአንጻሩ ቀሪዎቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከዋናው የአፍሪካ ፕሌት (Nubian Plate) ጋር በመጽናት አዲሱን የባሕር ዳርቻ በገጸ-በረከትነት ያገኛሉ።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ አዲስ በሚፈጠረው ባሕር ግራና ቀኝ የሚገኙ ሁለት የተለያዩ ግዛቶች ስለሚኖሯቸው 'የተቆራረጡ ግዛቶች' (Disconnected States) ተብለው ይጠራሉ።

ይህ የአህጉሩ መከፈል እንደ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ማላዊ እና ዛምቢያ ላሉ የባሕር በር ለሌላቸው (Landlocked) አገራት የራሳቸውን ወደብ የሚያጎናጽፍ በመሆኑ 'መከራው ያመጣው በረከት' (Blessing in Disguise) ይኖረዋል።

በተለይም ለኢትዮጵያ ሁለት ታላላቅ ለውጦችን ይዞ ይመጣል፦

አንደኛው፣ የተትረፈረፈ የባሕር በር ባለቤትነት ነው፦ አገሪቱ ሁለት ሰፋፊ የባሕር ጠረፎች ይኖሯታል፤ የምዕራባዊው የባሕር ጠረፍ ወደ 1,400 ኪ.ሜ፣ እንዲሁም ምሥራቃዊው ወደ 1,123 ኪ.ሜ ርዝመት ይኖራቸዋል። ይህ ክስተት ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿና ከዓለም ኃያላን ጋር የሚኖራትን ጂኦፖለቲካዊ ሚዛን ከመሠረቱ ይቀይረዋል።

ሁለተኛው ለውጥ፣ በውሃ የሚሸፈነው ግዙፍ የመሬት ስፋት ነው፦ ወደ 176,290 ስኩዌር ኪ.ሜ የሚሆን የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ገጸ-ምድር በሂደት በባሕር ውሃ ይዋጣል። በዚህም ሳቢያ የአፋር ክልል ከጥቂት ተራሮቹ አናት በቀር ሙሉ በሙሉ በውሃ ሲሸፈን፣ የሲዳማ ክልል (41%)፣ የደቡብ ኢትዮጵያ (37.2%) እና የሶማሌ ክልል (9.6%) መሬቶቻቸው የአዲሱ ባሕር አካል ይሆናሉ። እንደ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ እና አሳይታ ያሉ ከተሞችም የባሕር ወለል ይሆናሉ። የኦሮሚያ ክልል 8% የሚሆነውን መሬቱን በውሃ ቢነጠቅም፣ ክልሉ ወደ ምዕራባዊ (36%) እና ምሥራቃዊ (58%) መሬት ለሁለት ይከፈላል።

የባሕላዊ ዕውቀት ፋይዳ እና የአህጉሩ መቆረስ

ይልቁንስ፣ የአፋር ሕዝብ ከመሬት መንቀጥቀጥና ከእሳተ ገሞራ ክስተቶች ጋር በተያያዘ ያለውን ጥልቅ ባህላዊ ዕውቀት በጥንቃቄ ቢመረመር፣ በርካታ ጠቃሚ መረጃዎች ሊገኙ ይችላሉ።

ለምሳሌ፣ አፋሮች በኤርታ አሌ (Erta Ale) የሚገኘውን ተንቀሳቃሽ የላቫ ሐይቅ የኅብረ-ቀለማት ለውጥ በመመልከት ብቻ፣ መጪውን የድርቅ ሁኔታ ቀድመው የመተንበይ ባህላዊ ችሎታ እንዳላቸው ይታወቃል። ሆኖም ይህ ጅምር እንጂ ገና ያልተጠኑ በርካታ ምስጢሮች እንዳሉ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል።
gettyimages-587137028-612x612.jpg
The living lava lake in the crater of Erta Ale volcano, Afar region, Erta Ale, Ethiopia, on February 27, 2016, in Erta Ale, Ethiopia. Credit: Eric Lafforgue/Art in All of Us/Corbis via Getty Images
ለእዚህም በሃዋይ ደሴቶች የሚኖሩ ዜጎችን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል።

ልክ እንደ አፋሮች ሁሉ፣ የሃዋይ ተወላጆች ቋንቋ ከእሳተ ገሞራ ሂደትና ውጤቶች ጋር እጅግ የተሳሰረ በመሆኑ፣ የጂኦሎጂ ሳይንስ እንደ 'አአ' (aa) እና 'ፓሆሆ' (pahoehoe) ያሉ የሃዋይ ቋንቋ ስያሜዎችን በቀጥታ ከእነርሱ ተውሷል።

'አአ' የሚለው ስያሜ የመነጨው፣ አንድ ሰው በሾሉ የእሳተ ገሞራ ድንጋዮች ላይ በባዶ እግሩ ሲራመድ ከሚያወጣው “አ... አ...” የሚል የሕመም ድምፅ እንደሆነ ይነገራል። ይህ የሚያሳየው፣ ባህላዊ ዕውቀት ለዘመናዊ ሳይንስ ዕድገት ምን ያህል መሠረት ሊሆን እንደሚችል ነው።

አፋር ከፍተኛ ሙቀትና የዝናብ እጥረት ያለበት አካባቢ በመሆኑ፣ ድንጋያማ ተራሮቹ በአለት መሸርሸር (Weathering) ሂደት በፍጥነት አይለወጡም።
gettyimages-2113282171-612x612.jpg
A general view of the dry lava field of Erta Ale volcano, in the Danakil Depression of the Afar region, on March 23, 2024. In the heart of the Horn of Africa, the Danakil Depression is one of the hottest, most inhospitable places on earth, with temperatures topping 50 degrees Celsius. With much of its territory lying an average of 100m below sea level, this sparsely populated area of the Afar region hosts one of only a handful of volcanoes with an active lava lake, Erta Ale. It is littered with acid ponds, geysers and a deep crater with unearthly colours called Dallol. Credit: MICHELE SPATARI/AFP via Getty Images
ይህ ሁኔታ ዕፅዋት በቀላሉ እንዳይበቅሉ ስለሚያደርግ፣ ጂኦሎጂስቶች እነዚህን ተራሮች 'ራቁታቸውን የቀሩ ተራሮች' (Naked Mountains) ብለው ይገልጿቸዋል። እነዚህ 'ልብስ' አልባ ተራሮች እርቃነ-ሥጋቸውን ቆመው የምድርን የውስጥ ምስጢር ለዓይን የሚያሳዩ ታላላቅ የተፈጥሮ ምስክሮች ናቸው።

የአፍሪካ አህጉር ለሁለት የመቆረስ ሂደት ግን አንዳንዶች እንደሚገምቱት ፈጣን ክስተት አይደለም።

ፍጥነቱ በዓመት ከሰው ልጅ የጥፍር ዕድገት መጠን (ወይም በዓመት 20 ሚሊ ሜትር) አይበልጥም። ለምሳሌ ያህል፣ አዲስ አበባ ከተቆረቆረችበት ከ1880ዎቹ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ መካከል ያለው ርቀት የጨመረው በ10 ሜትር ገደማ ብቻ ነው።

በመሆኑም ምሥራቅ አፍሪካን ለሁለት ይከፍላል ተብሎ የሚጠበቀውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ስፋት የሚኖረው አዲሱ የባሕር ወለል ለመፈጠር፣ ከአራት ሚሊዮን ዓመታት በላይ እንደሚያስፈልገው መገመት ይቻላል።

የፖለቲካው ጩኸት የጋረደው የተፈጥሮ ድምፅ

ምሥራቅ አፍሪካ የምድር ንጣፎች (Plates) ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ በመወጠራቸው (Divergent plate boundary) ሳቢያ፣ ገጸ-ምድር ከሚቆረስባቸው የዓለማችን ግንባር ቀደም ስፍራዎች አንዱ ነው።

ይህንን ሳይንሳዊ ንድፈ-ሐሳብ በተጨባጭ ያረጋገጠ "ቀጥተኛና ፈጣን" መረጃ የተገኘው ደግሞ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በአፋር ምድር ነበር። በአጋጣሚ ሆኖ፣ ይህ ታላቅ ክስተት እውን የሆነው ኢትዮጵያ በምርጫ 97 ፖለቲካዊ ትኩሳት በታመሰችበት ወቅት ነበር።

በወቅቱ የምርጫውን ውጤት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ግጭትና ውጥረት የመገናኛ ብዙኃንን "ኦክስጂን" ጠቅልሎ የወሰደበት ጊዜ ነበር። መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም. ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ የነበረው ቅንጅት አራቱን አካላት አዋህዶ በይፋ ሲመሠርት፣ በተቃዋሚው ጎራ ከፍተኛ የድል አድራጊነት ስሜትና ተስፋ ነግሦ ነበር።

ሆኖም በሁለተኛው ቀን (መስከረም 16) አቶ ልደቱ አያሌው ውህደቱን በመቃወም ደብዳቤ አስገብተዋል በሚል በተሰራጨው አወዛጋቢ ዘገባ፣ የሕዝቡ ስሜት ከፍተኛ መደበላለቅ ገጥሞት ነበር።

መላው የሚዲያ ሠራዊት አቅሉንና ቀልቡን በዚህ ፖለቲካዊ ትኩሳት ላይ አድርጎ በነበረበት በዚያው ዕለት፣ በአፋር ክልል የ "ዳባሁ" (Dabbahu) እሳተ ገሞራ ፈንድቶ የ500 ሜትር ርዝመትና የ60 ሜትር ጥልቀት ያለው ግዙፍ ስንጥቅ ፈጥሮ ነበር።

ይህ ክስተት መላውን የዓለም ሳይንቲስቶች ሲያስደምም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን በፖለቲካው ጩኸት ምክንያት ለዚህ ታላቅ የተፈጥሮ ድምፅ ጆሮ ያዋሰ ሚዲያም ሆነ አካል አልነበረም።

የፖለቲካው ገጸ ምድር ስንጥቃት

ኢትዮጵያ የጂኦሎጂያዊ ውጥረቱ ሳይበቃት፣ ከበላዩ ተነባብሮ በሚገኝ አስጊ ፖለቲካዊ ችግር እየተወጠረች ትገኛለች።

እርግጥ ነው፣ ይህ ፖለቲካዊ ውጥረት እንደ መሬት መንቀጥቀጥ በንዝረት መጠን (Richter Scale) ወይም እንደ እሳተ ገሞራ በፍንዳታ መለኪያ (Explosivity Index) የሚገለጽ ላይሆን ይችላል።

ሆኖም ብሔርን፣ ሃይማኖትን እና ቋንቋን ከታሪክ ጋር ያወሳሰበው ይህ የማንነት ፖለቲካ ኢትዮጵያ አንድ ሆና እንዳትቀጥል የሚፈጥረው አደጋ፣ ከጂኦሎጂያዊው ስንጥቅ በብዙ እጥፍ ሊገዝፍና ሊፈጥን እንደሚችል ግልጽ ነው።

ምናልባትም የከርሰ-ምድሩን ውጥረት ያላላላን መስሎን፣ ሌላ የባሰ የፖለቲካ ውጥረት እየደረብንለት ይሆን?

እንዲያ ከሆነ፣ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው) የቋጠራት ግጥም ሁኔታውን በግሩም ሁኔታ ትገልፀዋለች፦ “ያሰብከው ዓላማ አልሆን ብሎ ሲከሽፍ፣ ሁኔታው ሲጠጥር፤ ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር።”

የዚህ ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ምንጭ ዘርፈ-ብዙ ቢሆንም፣ አሁን ካለው ሕገ-መንግሥታዊ መዋቅር የሚቀዳ መሆኑን የሚሞግቱ ወገኖች ጥቂት አይደሉም።

በተለይም የ1987ቱ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 39 ለእያንዳንዱ “ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ” ያለ ቅድመ-ሁኔታ የመገንጠል መብትን መፍቀዱ፣ ሕጉ የሚያመነጨው እምቅ ፖለቲካዊ ኃይል ወደ ውጭ (መገንጠል) ያተኮረ እንጂ፣ ወደ ውስጥ (አገራዊ ውህደት) የሚያማትር እንዳይሆን አድርጎታል።

ይህ ሁኔታ አገሪቱን ለዘላቂ ውጥረት አጋልጧታል። የአብርሃም ሊንከንን ታዋቂ ንግግር እዚህ ላይ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፦ “A house divided against itself cannot stand.” (“እርስ በርሱ የሚከፋፈል ቤት ጸንቶ ሊቆም አይችልም”)።

ይህ የመከፋፈል አዝማሚያ ካልታረመ፣ የከርሰ-ምድሩ ስንጥቅ አህጉርን ለመክፈል በሚሊዮን ዓመታት የሚፈጅበትን ያህል ሳይሆን፣ የፖለቲካው ስንጥቅ አገርን ለመበተን ጥቂት ዓመታት ብቻ ሊበቁት እንደሚችሉ አመላካች ነው።

በአሁኑ ወቅት በክልሎች፣ በዞኖችና በወረዳዎች መካከል የሚነሱ የይገባኛል ጥያቄዎች መበራከታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝብን ለጦርነትና ለግጭት ሲዳርጉ እየተስተዋለ ነው። ከእያንዳንዱ አዲስ ከሚፈጠር መዋቅር ጀርባ በማኅበረሰቡ መካከል መረር ያለ ውጥረት፣ የርስ በርስ ግጭትና እልቂት መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።

ቀደም ሲል በጥቂት የዓለማችን ስፍራዎች በታሪክ ድርሳናት ብቻ የሚጠቀሰው “ጄኖሳይድ” (የዘር ማጥፋት) የሚለው ከባድ ቃል፣ ዛሬ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ክስ መዝገቦች ውስጥ ተራ ቁልፍ ቃል እየሆነ መጥቷል።

በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በጌዴኦና በሌሎችም አካባቢዎች የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል የሚሉ ክሶች መደራረባቸው፣ የቃሉን አስደንጋጭነትና ክብደት እያሳጣው የመጣ ይመስላል።

በተጨማሪም አንዳንድ ክልሎች ራሳቸውን እንደ ሉዓላዊ አገር እየቆጠሩ መግለጫ ሲያወጡ ማየት፣ የአገሪቱ የግዛት አንድነት ወዴት አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሆነ ለመረዳት አቅጣጫ ጠቋሚ (GPS) የሚያሻው ጉዳይ አይደለም።

ይህ የመከፋፈል አዝማሚያ መነሻው የታሪክ ስህተትም ጭምር ነው።

ቀደም ሲል በማኅበረሰቦች መካከል ያለው ወሰን የሚተገበረው ግትር በሆነ ድንበር (Boundary) ሳይሆን፣ በሰፊ ቦታ ላይ በሚከናወን አዝጋሚ የሽግግር ጠረፍ (Frontier) ነበር።

አውሮፓውያን ለአፍሪካውያን የሰመሩት ግትርና ሰው ሰራሽ ድንበር፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ለክልሎች መዋቅር እንደ ሞዴል መወሰዱ ተፈጥሯዊውን የሽግግር ጠረፍ ሕግ የሚጻረርና ለግጭት መንስኤ የሆነ የመከፋፈል አጥር ሆኗል።

ዳንኤል ካሳሁን (ፒ ኤች ዲ) በመሬት-ነክ ጉዳዮች የተለያዩ መጣጥፎችን የሚያበረክቱ ሲሆን በኦስተን / ቴክሳስ የጂኦስፓሻል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው daniel.kassahun@gmail.com ይገኛሉ፡፡

Share

12 min read

Published

By Daniel Kassahun (PhD)

Source: SBS



Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service