ዛሬ እሑድ ሴፕቴምበር 13 - 2020 "ግድቡ እንዲጠናቀቅ የበኩሌን አስተዋፅዖ አደርጋለሁ፤ ለትውልድ አሻራዬን አስቀምጣለሁ" በሚል መሪ ቃል ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክት ማስፈጸሚያ የሚውል የገንዘብ አስተዋፅዖ ለማበርከት በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የታደሙበት የዙም ስብሰባ ተካሂዷል።
በውጤቱም ኢትዮጵያውያኑ የዙም ስብሰባው እስካከተመ ድረስ ለግድቡ ማሰሪያ የሚያግዝ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከ$232 ሺህ 550 የአሜሪካ ዶላርስ ተሰብስቧል። ቀጣይ የገቢ ማሰባሰብ ሂደትም በየስቴቱ በመቀጠሉ በሳምንት ውስጥ ጠቅላላ መዋጮዎቹ በ በአራት ሰአት ተኩል ጊዜያት ውስጥ በተሰባሰበው ላይ እንደሚጨምር ይጠበቃል። የገቢ አሰባሳቢ ግብረ ኃይሉም ጠቅላላ ገቢዎቹን አጠናቅቆ ያስታውቃል።
በዚሁ ዕለት የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ ነዋሪ ለሆኑ ኢትዮጵያና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ንግግር "በቦንድ ሽያጭ፣ በስጦታና እንዲሁም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ላደረግነው ጥረት ላበረከታችሁትና እያበረከታችሁ ላላችሁ ሁሉ በኢፌዴሪና መንግሥትና በራሴ ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት ለማስመስከር አስተዋፅዖ አድርጓል። ግድቡ ለአገራችን የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም። ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያላት ሉዓላዊ መብት በምንም የሚተካ አይደለም። ግድቡን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን" ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት ለማስመስከር አስተዋፅዖ አድርጓል።
ሚኒስትር ደጉ በንግግራቸው ማጠቃለያ "በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የምትኖሩ ጥሪያችንን ተቀብላችሁ ቦንድ በመግዛት፣ በዕውቀታችሁ፣ የኢትዮያን አቋም ለሚመለክታቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በማስረዳት በምትችሉት ሁሉ አገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ" ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በዕለቱ የሃይማኖት አባቶች ተገኝተው ቃለ ቡራኬ አሰምተዋል። ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ አውስትራሊያ ና የሲኖዶስ አባል

Source: PD
"የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ከተስፋ አልፎ የተጨበጠ አገልግሎት እንዲሆን ተመኝተው፤ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ታሪክ ተክለን የምናልፍበት አጋጣሚ ነው። የድል ውጤትም ነው" ሲሉ ተሳታፊዎች በዕውቀት፣ በገንዘብና በተቻላቸው አቅም ሁሉ አሻራቸውን እንዲያኖሩ አበረታተዋል።
በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን እስልምና ሃይማኖት መሪ ኢማም ሼህ አብዱራህማን ከቢር በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብን ከጅምሩ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ያደረሱትን በማመስገን ከግድቡ ባሻገር ኢትዮጵያ ለታላቅ ደረጃ እንዲደርስ ተመኝተዋል።
ዶ/ር ፓስተር ናትናኤል ገመዳ - የዘጸዓት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ዋና መጋቢም በበኩላቸው ወቅቱ የስኬትና የመግባባት እንዲሆን የአንድነትና የፍቅር መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቀጣይነትም "ግድቡ እንዲጠናቀቅ የበኩሌን አስተዋፅዖ አደርጋለሁ፤ ለትውልድ አሻራዬን አስቀምጣለሁ" በሚል መሪ ቃል በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ያካሄዱትን የዙም ስብሰባ ያስተባብረው በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ሕዳሴ ገቢ ማሰባሰቢያ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ አያሌው ሁንዴሳ "የታደምነው መተኪያ የሌላት አገራችን ላደረገችልን ጥሪ የተግባር ምላሽ ለመስጠት ነው" ብለዋል።
አያይዘውም "ኢትዮጵያ የቆመችው በገንዘብ መዋጮ ሳይሆን በደምና አጥንት መዋጮ ነው፤ ልማቷን በገንዘብ ማገዝ የመጨረሻው ትንሹ ነገር ነው በማለት" ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የተቻላቸውን ያህል ለሕዳሴ ፕሮጄክት ማስፈጸሚያ እገዛ እንዲያደርጉ አበረታተዋል።
አቶ በሪሁን ደጉ - በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ስልጣን ሚኒስትርና ምክትል ሚሽን መሪ ፤ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያውያን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የገንዘብ ችሮታ በማድረግና ሙያዊ ዕውቀታቸውን በማጋራት ላደረጉት አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል።
አክለውም፤ የግድቡ ጅማሮ ከፍጻሜ እንዲደርስ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የንዋይና የሙያ እገዛቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ አድርገዋል።
የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ግርማ ፈይሳም ስለ ቦንድ ሽያጭ፣ አጠቃቀም፣ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታና ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የሚያበረክተውን የፋይናንስ እገዛ ለታዳሚዎች አስረድተዋል።
የዕለቱን ፕሮግራም በጋራ ሲመሩ የነበሩት ማርታ ጸጋውና አቶ ብሩክ በየዝግጅቶቹ መካከል ስለ ሕዳሴ ግድብ አንኳር የሆኑ መረጃዎችን አቅርበዋል።
እንዲሁም፤ በዓባይ ወንዝ ላይ የሶስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ከፍያለው መኮንን የሕዳሴ ግድብ ፋይዳን አስመልክቶ ለታዳሚዎች ሙያዊ ገለጣ አድርገዋል።
Share

