ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ።
ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ይህን ያስታወቁት በአፍሪካ ኅብረት በኩል በኮንጎ ኪንሻሳ የተደረገውን የሦስትዮሽ ድርድር በሚመለከት በዛሬው ዕለት በሰጡት ማብራሪያ ነው።
በድርድሩ በታዛቢነት የሚሳተፉ አካላት የአደራዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው በግብጽ እና ሱዳን የቀረበውን ሐሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓንም ተናግረዋል።
በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በሚካሄደው የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ደቡብ አፍሪካ በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል።
በመሆኑም ግድቡ ድርድር ላይ እነዚህ በታዛቢነት የሚሳተፉ አካላት ከታዛቢነት ባለፈ የአደራዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው ግብጽ እና ሱዳን ሐሳብ ማቅረባቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በድርድሩ ግብጽ እና ሱዳን ተጨማሪ ታዛቢ እንዲገባ እና ያሉትን የታዛቢዎች ሚና ለመቀየር ያሳዩትን ፍላጎት ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው በማሳወቅ ውድቅ አድርጋዋለች ብለዋል።
ግብጽ እና ሱዳን በተለይም ደቡብ አፍሪካን ከታዛቢነት ለማስወጣት ያደረጉትን ጥረትም መቃወሟን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ታዛቢዎቹ በድርድሩ ጣልቃ ሳይገቡ የታዛቢነት ሚናቸውን ለሁሉም ተደራዳሪዎች ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ሦስቱ ሀገሮች መስማማታቸውን እንደገለጹ ኢዜአ ዘግቧል።

