የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬ ማክሰኞ ከቀትር በኋላ መካሄድ እንደሚጀምር ገልጠዋል።
ምንም እንኳ ቃል አቀባዩ በድርድሩ ላይ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ጉዳይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ቢገልጡም በግብፅ የዜና አውታሮች የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ቀደም ብሎ በተያዘ የውጭ አገር ጉዞ ፕሮግራም ሳቢያ ምናልባትም በስብሰባው ላይ ላይታደሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የግብፅ የውኃና የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ ኤል-ሳባይ በበኩላቸው ግብፅ በስብሰባው ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንደምታደርግና ልዩነቶችን ፈጥረው ባሉት ሕጋዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ እንደምታተኩር ገልጠዋል።
የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ ሱዳን ሙሉ ተሳትፎ እንደምታደርግና ድርድሩን ከእልባት ላይ ለማድረስ የሚያግዝ አዲስ የመደራደሪያ ማዕቀፍ ይዘው እንደሚቀቡ ተናግረዋል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየው የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ለሰባት ሳምንታት ሲካሄድ ቆይቶ በግብፅ የውኃ ሙሌትና አስገዳጅ ድንጋጌ እከላ ጥየቃ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከተካሄደው የበይነ መረብ ውይይት በኋላ መቋረጡ የሚታወስ ነው።
አምባሳደር ዲናም በፊናቸው ኢትዮጵያ በሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና መብት ባስከበረ መልኩ ድርድሩን እንደምታካሂድ ገልጠዋል።
የሶስትዮሽ ድርድሩ ስኬታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ ፅኑ ፍላጎት እንዳላትም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

