የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማክሰኞ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም ለውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ወቅት ቢልለኔ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል በግንባር ሆነው አመራር እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል። “በዚህም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ የተደቀነውን ስጋት የመመከቱ ተግባር ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ነው፤ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች በሕወኃት ተይዘው የነበሩ ስፍራዎችን እያስለቀቁ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሕወኃት አስገድዶ ያሰለፋቸው የትግራይ ወጣቶች ጦርነቱ እያለቀ መሆኑን ተገንዝበው ለመንግስት የፀጥታ አካላት እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል” ብለዋል፡፡

ቢልለኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጦር ሜዳ ሄደው ጦሩን መምራት ከጀመሩ አንድ ሳምንት እንደሆነ ገልፀው የጠቅላይ ሚንስትሩን ወደ ጦር ግንባር መሄድ ምዕራባውያን በተሳሳት መንገድ መረዳታቸውንም ተችተዋል፡፡ ወደ ጦር ግንባር የሄዱት ጦርነቱ ተባብሶ በመቀጠሉ እንዳልሆነ የጠቀሱት ቢልለኔ ይልቁንም ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ለመውጣት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር መገኘት የሠራዊት አባላት ሞራልን ከፍ ማድረጉ እና በዜጎች ዘንድም ህብረት መፍጠር ማስቻሉን ጠቅሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መደበኛ ሥራቸው የሚለሱበትን ጊዜ ግን አስረግጠው መናገር እንደማይችሉ ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና ቢልለኔ እንዳሉት ሕወኃት የኢትዮጵያ ሰላም እና ደህንነት አደጋ መሆኑ እስኪያበቃ ድረስ እርምጃው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በመግለጫቸው ትኩረት ከሰጡት ጉዳይ አንዱ የትዊተር ማህበራዊ ትስስር ገፅ የተመለከተው ሲሆን ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾች እየታፈኑ በሌላ መልኩ ሕወኃትን የሚደግፉና ሀሠተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩት ግን ተፈቅዶላቸዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ለዚህም በትዊተር ውስጥ የሕወኃት ደጋፊዎች ስለመግባታቸው ለተቋሙ የፖሊሲ ቡድን ሪፖርት አድርገናል ብለዋል፡፡
ቢልለኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የሚፈለገውን ውጤት እያስመዘገበ ነው ያሉ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄዱ ፍተሻዎች ጦር መሳሪያዎች፣ ወታደራዊ መሳሪያዎች፣ የደንብ ልብሶች፣ የተለያዩ አገራት የደንብ ልብሶች፣ መገናኛ መሳሪያዎች እና ሐሰተኛ መታወቂያዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ጦርነቱን ተከትሎ 1.1 ሚሊዮን ሕዝብ መፈናቀሉን እና 5.6 ሚሊዮን ያህሉል ደግሞ በግጭቱ ምክንያት መጎዳታቸውን የተናገሩት ቢልለኔ በተመሳሳይ በአፋር ክልል ተጎጂ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከ260ሺህ በላይ ሆነዋል ብለዋል። የፌደራል እና ክልሎቹ አደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽኖች ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ለተጎጂዎች የሰብዓዊ እርዳታ እያቀረቡ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ወደ ትግራይ ክልል እህል የጫኑ ተሸከርካሪዎች መጓዛቸውን አሳውቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሕወሓት በኩል ኖቬምበር 30 ማለዳ ላይ የተከዜ ሃይድሮኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ የአየር ጥቃት እንደደረሰበት በቲዊተር ገጻቸው ገልጠዋል።
(ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ)
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሰኔ 29 ቀን 2005 ዓ.ም ለዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን የሰጠውን የክብር ዶክትሬት መሰረዙን አስታወቀ ።
የዩኒቨርሲቲው ለዶ/ር እሌኒ የክብር ዶክትሬት ሰትቶ የነበረው "የሕብረተሰቡን አኗኗር እና የሀገሪቱን የውጭ ንግድ ስርዓት እንዲሻሻል ባበረከቱት መልካም አስተዋጽኦና ለወደፊቱም በተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት ልክ ሀገሪቱ ያለአድሎና በእኩልነት እንዲያገለግሉ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አምባሳደር ሆነው እንዲያገለግሉ" መሆኑን ገልጧል።፡
አያይዞም፤ ዶ/ር ኢሌኒ ሰሞኑን የዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ማዕከል አዘጋጅቶት በነበረው የበይነመረብ ስብሰባ ላይ "አድሏዊ፣ የአንድን ቡድን ፍላጎት ብቻ ያንጸባረቀ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን ዋና ዋና እሴቶች የሚፃረር ሀሳብን በማራመዳቸው" የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ለዶ/ር ኢሌኒ ገብረመድህን ሰጥቶት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መሰረዙን አስታውቋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሰኔ 29 ቀን 2005 ዓ.ም ለዶ/ር ኢሌኒ ዘውዴ ገ/መድኅን የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በማቋቋምና በመምራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጣቸው መሆኑ ይታወሳል፡፡

