የመንሥት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ለመንግድድት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት የቀጥታ ስርጭት መግለጫ እንዳሉት “በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እየተመራ በሁሉም ግንባሮች ወደ ከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የገባው የ"ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" ከፍተና ውጤቶችን ማስመዘገቡን ገለጡ፡፡
ዶር ለገሰ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባለው በጋሸና ግንባር የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል ሚሊሻና ፋኖ በጥምረት ባደረጉት ተጋድሎ የአርቢትን፣ የአቀትን፣ የዳቦና የጋሸና ከተሞችን ነጻ ማውጣቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶር ለገሰ ገለፃ “በዚህ ግምባር ሕወሓት ለበርካታ ወራት በወረራ የያዘውን አካባቢ ህዝብ በማስገደድ ያሰራውን ባለብዙ እርከን ኮንክሪት ምሽግ በተቀናጀ እቅድ፣ አመራርና ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአነስተኛ መስዋዕትነት ምሽጉ ተሰብሯል። በዚህ ግንባር በርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን ከባድ መሳሪያዎች በወገን ጦር ተማርከዋል።” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ጋሸናን መቆጣጠሩ ሕወሓት በላሊበላ፣ ወልዲያና ደሴ የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቆጣጠር መንገዱን ምቹ ያደርጋል ሲሉም አክለዋል።
በሌላ መልኩ በወረኢሉ ግንባር የጃማደጎሎ ወረኢሉ ገነቴ፣ ፊንጮፍቱ፣ አቀስታ ከተሞች ነጻ ወጥተዋል ያሉት ዶር ለገሰ በሸዋ ግንባር ደግሞ የመዘዞ፣ ሞላሌ፣ ሸዋሮቢትና አካባቢው እንዲሁም ራሳና አካባቢው ነፃ ወጥተው ወደፊት እየገሰገሱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
በምስራቅ ግንባርም የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ባደረጉት ተጋድሎ ነጻ የወጡት የካሳጊታ፣ ቡርቃ ዋኢማ ጪፍቱ ድሬሩቃ፣ ጭፍራ አለሌ ሱሉላ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወደ አካባቢው አስተዳደር ተመልሷል ብለዋል፡፡
ከደቂዎች በፊት በሶሻል ሚዲያ ገፆቸው መልዕክት ያሰፈሩትና በግንባር የሚገኙት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ዐቢይ አህመድ "የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁሉም መስክ ተባብሮ ሲነሣ ውጤቱ ድል ነው። በግንባር፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በኮሙኒኬሽን፣ በስንቅ ዝግጅት፣ ዘማች በመከባከብ፣ ጸጥታ በማስከበር፣ተፈናቃዮችን በመደገፍ. በሁሉም ግንባሮች ለዘመታችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል፡፡
በመንግሥት በኩል የተሰጠውን ወታደራዊ መግለጫ አስመልክቶ ለጊዜው በሕወሓት በኩል የተሰጠ ምላሽ አልቀረበም።
(ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ)