ኢትዮቴሌኮም ሰኞ ጥር 23 - 2014 በሐያት ሬጄንሲ ሆቴል ለጋዜጠኞች የስድስት ወራት አፈፃፀሙን አስመልክቶ ባዘጋጀው መግለጫ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ኩባንያቸው 28 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቀዋል።
ይህም ከእቅዱ አንፃር 86.4 በመቶ መሆኑ ነው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ የገለፁት። ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ6.7 በመቶ እድገት አሳይቷል ብለዋል።
እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገለፃ ኩባንያው የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች ብቻ 74.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም ገልፀዋል። አክለውም የደንበኞችን ቁጥርም 61 ሚሊዮን ገደማ በማድረስ የተቋሙን የግማሽ ዓመት ዕቅድ ሙሉ በሙሉ እንዳሳኩ ተናግረዋል።
ወ/ሪት ፍሬሕይወት አዲስ የዲጂታል ፋይናንሲግ ሲስተማቸው የቴሌብር ደንበኞች ቁጥርም 13.1 ሚሊዮን መድረሱን የጠቀሱ ሲሆን።
አጠቃላይ የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኛቸው ቁጥር 58.7 ሚሊዮን እንደደረሰ ያብራሩት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ በ136 ከተሞች የ4G LT አድቫንስድ አገልግሎት መዘርጋቱንም ተናግረዋል።
ለኩባንያቸው ፈታኝ ወቅት እንደነበረ ያብራሩት ወይዘሪት ፍሬሕይወት በጦርነትና በግጭት ምክንያት ከፍተኛ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ውድመትና ጉዳት እንዲሁም የአገልግሎት ገቢ መቋረጥ አጋጥሟል ብለዋል። በ3,473 የሞባይል ጣቢያዎች ምሶሶዎች ላይ የአገልግሎት መስተጓጎልና አደጋ ማጋጠሙን ያብራሩ ሲሆን በዚህም በ6 ወራት ውስጥ ኩባንያቸው 3.67 ቢሊዮን ብር ገቢ አጥቷል ብለዋል።
የወደሙ ንብረቶችን ለመተካትና አግልግሎት ለማስጀመር የወጣው 328.9 ሚሊዮን ሲታከልበት የጦርነቱ ዳፋ ከ 4 ቢሊዮን ብር እንደሚልቅ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በፀጥታ ችግር ትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የአማራና አፋር አካባቢዎች አገልግሎት መስጠት ያልተቻለባቸው ወረዳዎች እንደሚገኙ ያሳወቁት ፍሬሕይወት
በአካባቢዎቹ ላይ ያለው የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች እስካሁን ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳልተቻለ ገልፀዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫቸው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ትልቅ ስኬት አድርገው የገለፁት የኩባንያቸው ውዝፍ የኦዲት ሪፖርት መጠናቀቁን ነው። የዓለምአቀፍ ኦዲት ደረጃን ባሟላ ሁኔታ " እንከን የለሽ " በሚል ምድብ የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት ግኝት ላይ መድረሳቸውን የገለፁ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ ኩባንያቸው ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት አሉታዊ ዝርዝር ውስጥ ለማስወጣት እንቅስቃሴ እንደሚጀምሩ አብራርተዋል።
ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነታችሁ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል በሚል ከSBS አማርኛ ዘጋቢ ለቀረበላቸው ጥያቄም "በአፍሪካ ሀገር በቀል የሆነ የቴሌኮም ኩባንያ ያለን ብቸኛ ሀገር ነን ፡ ይህንን እንኮራበታለን። ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነታችንን ለማጠናከርም አንዘናጋም። የተወዳዳሪዎቻችንን አቅምና ቴክኖሎጂ ከግምት በማስገባት ጥራቱን የጠበቀ አስተማማኝ አገልግሎት ለደንበኞቻችን ለመስጠትና ከየትኛውም የቴሌኮም ጋር የተያያዘ ጉዳት ሀገራችንን ለመጠበቅ እንሰራለን" ብለዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]

