በ "ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሸዋ፣ ጋሸናና ወረኢሉ ግንባሮች ቀደም ሲል በሕወሓት ስር የነበሩ ከተሞች በመንግሥት ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኩል የተሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
በዚህም መሠረት፤
- በሸዋ ግንባር የቀወት ወረዳ፣ ለምለም አምባ፣ ጀውሃ፣ ሰንበቴ፣ አጣየና ካራ ቆሬ ከተሞች
- በጋሸና ግንባር ኮንና ዳውንት ሙሉ በሙሉ
- በወረኢሉ ግንባር ልጓማ ከተማ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሆነዋል።
በሌላም በኩል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ በሕወሓት ስር የነበሩት የመሃል ሜዳ፣ ጨፋ ሮቢት፣ ሐርቡና መኮይ ከተሞች በመንግሥት ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጧል።
ሕወሓት
የሕወሓት ጦር አዛዥ የቀድሞው ሌ/ጂኔራል ታደሰ ወረደ በጦራቸው ስም ለትግራይ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት በጦርነት ወቅት ወደ ፊት መራመድና ወደ ኋላ መጓዝ ያለ ክስተት መሆኑን አመልክተዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥም በቁጥጥራቸው ስር የነበሩትን ሥፍራዎች ለቅቀው መሔዳቸው ተጋላጭነትን ከመቀነስ አኳያ በፈቃደኘነት የሆነ እንጂ በወታደራዊ ኃይል የበላይነት ግድ ተሰኝተው እንዳልሆነ የጠቀሱት የጦር አዛዥ "አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ስንሔድ፤ ነገ ሁለት እርምጃ ወደ ፊት እንደምንራመድ እናውቃለን" ብለዋል።
አያይዘውም ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን አመኔታ ገልጠዋል።

