የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ከዚህ ዓለም ተለዩ።
ፓትሪያርኩ ለሕልፈተ ሕይወት የበቁት ትናንት ሐሙስ የካቲት 24 ምሽት ነው።
አቡነ መርቆርዮስ ከሕልፈተ ሕይወታቸው በፊት በሕክምና እርዳታ ላይ ይገኙ ነበር።
ብፁዕነታቸው ነሐሴ 29, 1980 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 4ኛ ፓትሪያርክ ሆነው የተሰየሙ ሲሆን፤ በ1983 ለስደት ተዳርገዋል።
ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ የሰደት መንፈሳዊ ግልጋሎት በኋላም ወደ አገረ ኢትዮጵያ ሐምሌ 25, 2010 ተመልሰዋል።
ፓትሪያርኩን ከስደት ወደ አገረ ኢትዮጵያ ይዘው የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ዓርብ የካቲት 25, 2014 ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ፤
"አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ማረፋቸውን በመስማቴ ጥልቅ ኅዘን ተሰምቶኛል። ተለያይተው የነበሩት ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ እንዲሆኑ ቅዱስነታቸው ወሳኙን ሚና መጫወታቸውን አስታውሳለሁ። ነገሮችን በአርምሞ እየተመለከቱ ሀገራችንን በጸሎት ያግዙ ነበር። በዚህ ወቅት እሳቸውን ማጣት ከባድ ጉዳት ነው። ለሁላችንም መጽናናትን እመኛለሁ" ብለዋል።
የምስራቅ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዛሬ የካቲት 25 ቀን 2014 ከሜልበርን - አውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ዕረፍትን አስመልክቶ የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።
“በአማን መርቆሬዎስ”
ሀገርና ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ባሉበት በዚህ ወቅት የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያን ህልፈት ለቤተ ክርስቲያን ልጆች ታላቅ ሀዘን ነው። ብጹዕ ወቅዱስ አባታችን ለሀገር በረከት ለቤተ ክርስቲያን ሞገስ ነበሩ።
በዚህ ሚዲያው ሀገሩን ሁሉ በሞላበት ዘመን እንደ ነቢዩ ሙሴ፤ እንደ ኤርምያስና ቅዱስ አጋቶን መናገር እየቻሉ አንደበታቸውን ገተው በአርምሞና በጸሎት ለዘመናት ተወስነው መኖራቸው ዕፁብ ድንቅ ነው። ስለሆነም በአርምሟቸውና በትዕግስታቸው ዓለምን ድል ነስተውት በክብር አረፉ።
ቅዱስነታቸው ለገዳማትና ለአድባራት የልማት ሥራ በማቋቋም የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ባዶ እንዳትቀር በጨለማ ለነበሩ የአብነት መምህራን ቋሚ ደመወዝና ለተማሪዎቻቸው እርዳታ በማድረግ ብርሀን ሲያወጡ በዓለም ለተበተነው ኢትዮጵያዊም ተስፋ ነበሩ። በአጠቃላይ በውስጥም በውጭም ለነበርችው ቤተ ክርስቲያን መሰረትና አምድ የነበሩ ሲሆን ለጴጥሮስ የተሰጠውን የበጎችን አደራ በፍጹም ትዕግስት የፈጸሙ ቅዱስ አባት ነበሩ።
ትላቅ ሰውና ትልቅ ዛፍ ስሩ በምድር ሀረጉም በሰማይ ነው። ቅዱስነታቸው እንደ እንጦንስ በጸሎት እንደ ቅዱስ ያሬድ በማህሌት እንደ ቄርሎስ በመጻህፍት የሚያጽናኑን አባት ስለነበሩ ሀዘኑ አስፈሪ ቢሆንም በተመኙትና እግዚአብሔር ባዘጋጀቸው ዓለመ ቅዱሳን በማረፋቸው እንጽናናለን።
ቅዱስነታቸው እንደ ኖኅ የሰላምና የእርቅ ምልክት ነበሩ እንደ ሄኖክ መገለጥና መታየት ባህሪያቸው አልነበረም። ሁሉን በትህትና በፍቅርና በአርምሞት ሆነው “ድልዋኒክሙ ነበሩ” እያሉ ያሳልፉት ነበር። በዝምታ ውስጥ እግዚአብሔርን፤ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን አስታርቀው ኃላፊውን ዓለም ትተው ወደ አምላካቸው ደስታ ገብተዋል።
አቤሜሌክ “የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየኝ” ብሎ እንደጸለየ ቅዱስነታቸውም የኢትዮጵያንና የቤተ ክርስቲያንን መከራና ጥፋት አታሳየኝ እያሉ እስከ እለተ ህልፈታቸው ይጸልዩ ነበር ዛሬ ግን ድካምና መከራ ከበዛበት ዓለም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ ዓለመ ቅዱሳን ተሸጋግረዋል።
ቅዱስነታቸው እንደ ነቢዩ ነህምያ በሥራ ትጋታቸው፤ በፍትሕ አዋቂነታቸውና በአስተዳደር ብቃታቸው ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ምሳሌ ነበሩ። ቅዱስነታቸው ለችግረኞች አባት፤ ለተበደሉ ፍትህን የሚሰጡና ለተረሱ አስታዋሽ ነበሩ።
የቅዱስ ልጅ ቅዱስ ነው የጻድቅም ልጅ ጻድቅ ነው የነቢይ ልጅም ነቢይ ነው ስለሆነም ሁላችንም የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደ አባታችን አርሞምንና ትዕግስትን ተላብሰን በጸሎት እየተጋን ይህን የፈተና ጊዜ እንድናሳልፍ አደራ እንላለን። እግዚአብሔር ያዘኑትን ያረጋጋልን ሕዝብንና ቤተ ክርስቲያናን ይጠብቅልን። የቅዱስነታቸው በረከት ይደርብን።
በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ የምስራቅ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

