የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኦሮሚያ ቄሌም ወለጋ ዞን የደረሱት የጭፍጨፋ ሪፖርቶች በእጅጉ ያሳሰቡት መሆኑን ጁላይ 4 / ሰኔ 27 ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ አስታወቀ።
አያይዞም፤ ለጊዜው ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥርን አስመልክቶ ሙሉ የማረጋገጫ ድምዳሜውን ይፋ ባያደርግም በኦሮሚያ ሐዋ ገላን ወረዳ ቄሌም ወረዳ ዞን መንደር 20 እና መንደር 21 ውስጥ የደረሰው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ግና በብርቱ አሳሳቢ መሆኑን ገልጧል።
ኮሚሽኑ ሁኔታዎችን መከታተሉን እንደቀጠለ መሆኑንና ከጭፍጨፋው ከተረፉት ሰዎችና ከአካባቢው የመረጃ ምንጮቹ ጋር እየተነጋገረ ያለ መሆኑን አመላክቷል።
በመረጃ ምንጮቹ መሠረትም ጥቃት ፈፃሚዎቹ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ወይም ኦነግ ሸኔ በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን እንደሆነና ግድያዎቹ የተካሔዱትም ሰኔ 27 ከቀትር በፊት እንደሆነ የደረሱት ሪፖርቶች ማመልከታቸውን ገልጧል።
ኢሰመኮ የመንደር 20 እና 21 ነዋሪዎች የአማራ ዝርያ ያላቸው መሆኑን እንደተገነዘበና የመንግሥት ፀጥታ ኃይላትም በሥፍራው መድረሳቸውን አመልክቷል።
ሆኖም ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቀዬ መጠጊያ ፍለጋ ላይ እንደሆኑም ጠቁሟል።
የኮሚሽኑ ዋና ኃላፊ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ድርጊቱን አስመልክተው “በአካባቢው ሰፍኖ ያለው የደኅንነት ስጋትና ዘር ተኮርነትን የተላበሰው የነዋሪዎች ግድያ በአስቸኳይ ሊገታ ይገባል" ብለዋል።
የኮሚሽኑን ጥሪ ዳግም በማስተጋባትም ሌላ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት እንዳይቀጠፍ የመንግሥት ፀጥታ ኃይላት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስድ አፅንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።