የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 3ኛ ዙር ሙሌት ከመጪው ሐምሌ ወር አንስቶ መከናወን እንደሚጀምር አንድ ስማቸው እንዲገለፅ ያልወደዱ የግድቡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊን ዋቢ አድርጎ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።
ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ ወደ ግድቡ የሚፈሰው የውኃ መጠን ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ከፍ እያለ ከሄደ በኋላ ወደ ግድቡ የሚገባውን ውኃ በመያዝ በሐምሌ ወር ሙሌቱ ይጀመራል ብለዋል ኃላፊው።
በዚህ ዓመት ወደ ግድቡ እንዲገባ የሚጠበቀውን የውኃ መጠን ለመያዝ የግድቡን ቁመት የመጨመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል። የውኃ ሙሌቱ ሲጀመር የግድቡ ቁመት በሚፈለገው መጠን እንደሚደርስ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በሰኔ ወር መጨረሻ ሲጀመር በነሐሴ ወር አጋማሽ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ በዓመቱ በነበረው ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ፍሰት የተነሳ መጠናቀቁ የተበሰረው ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር።
[ሪፖርተር]
የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኮቲዲቯር አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከማላዊ አቻው ጋር ተጫውቷል።
ይህ የማጣሪያ በማላዊ መዲና ቢንጉ ብሄራዊ ስታዲየም ተካሂዶ ዋሊያዎቹ ከ ማላዊ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2 - 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።
የማላዊውን የማሸነፊያ ሁለት ግቦች ጋባዲንሆ ምህንጎ አስቆጥሯል ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ከሽንፈት ያልታደገችውን ግብ የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር አስቆጥሯል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የፊታችን ሀሙስ ምሽት 1:00 ከግብፅ አቻው ጋር ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እንደሚያከናውኑ የካፍ ድረገጽ የጨዋታ መርሃ ግብር ያስረዳል።

