ንቅናቄው በምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ አሰቃቂ ጥቃት መፈፀሙን ረቡዕ ሰኔ 29 ባወጣው መግለጫ ገልጧል።
አብን "ይህ ጥቃት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲፈፀም አዲስ አይደለም፤ ይልቁንስ የተሳሳተው ትርክት አንዱ ቅርንጫፍ ነው" ሲል አስታውቋል።
የንቅናቄው ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው "አማራ ጠል ትርክት ከውጭም ከውስጥም ጠላት አፍርቶልናል እናም በዚህ ደግሞ እየተጎዳ ያለው ምስኪን ራሱን መከላከል የማይችል ሕዝብ ነው፤ የአሁኑን ጨምሮ ተከታታይ ችግሮችን ለማስቆም የሚመለከታቸው ሁሉ ሊያስቆሙት ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።
አክለውም "በአማራ ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለውን ዘር የማጥፋት ጥቃት የሚመለከታቸው ሁሉ ሊያስቆሙት ይገባል፤ ንቅናቄው በአማራ ሕዝብ ላይ አየተፈፀመ ያለው ስልታዊ ዘር ማጥፋት ነው ብሎ" ሲሉም ገልጠዋል።
አብን፤ የአማራ ሕዝብ ተከታታይ ግድያ ግድ ሊለው የሚገባው የመንግስት መዋቅር ችላ ማለቱን እንዲያቆም እና ባስቸኳይ ሕዝብን እንዲጠብቅ በማለት ያሳሰበ ሲሆን፤ አያይዞም "ጥቃቱን እየተከታተለ እርምጃ ያልወሰደው መንግስት ይህንን ጥቃት እየሸፈኑ ያሉ እንዲሁም ሕዝብን መጠበቅ ያለባቸው ከክልል እስከ ፌደራል ቢሮዎች ተጠያቂ ናቸው" ሲልም አብን አስታውቋል።
አክሎም፤ ጥቃቱን ለማስቆም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅና የአካባቢው ነዋሪዎች በፀጥታ አካልነት ተካትተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችል ሥራ እንዲሰራ አብን ጠይቋል።
አብን አጥቂዎች በግልፅ ፍርድ እንዲበየንባቸው፤ ይህን ችላ ያሉ፣ እንዲባባሱ ያደረጉ ሚዲያዎች፣ ፓለቲከኞች እና ግለሰቦችን መንግስት ተጠያቂ እንዲያደርግና ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅም ጠይቋል።
ንቅናቄው "አማራ የመጣበትን ችግር ለመመከት እንደ ሕዝብ በአንድነት ለመመከት አንድነቱን ጠብቆ የመጣውን የዘር ማጥፋት ጥቃት ለመመከት እንዲሠራ' ሲል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ በመጪው ሐሙስ የሐዘን ቀንን ለማሰብ የሻማ ማብራት፣ የፓናል ውይይት እና ሌሎች ዝግጅትን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጧል።
ምንጭ AMC