የዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) ለኢትዮጵያ ሰብዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍተኛውን የጥራት ዕውቅና ደረጃ ሰጠ

*** የዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) 118 ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት የሆኑ አባላት ኅብረት ሲሆን ከፓሪስ ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት መመሥረትንና መጠናከርን የሚያበረታታ ነው።

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Cpmmission.

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Cpmmission. Source: D.Bekele

የዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍተኛውን የጥራት ዕውቅና " A " ደረጃ ( Accreditation ) ሰጠ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለSBS አማርኛ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከጠንካራ የግምገማ ሂደት በኋላ የሚሰጠውን የዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (Global Alliance of National Human Rights Institutions (GANHRI)) የደረጃ “A” (አንደኛ ደረጃ) እውቅና ማግኘቱ ኮሚሽኑ የፓሪስ መርሆችን ሙሉ በሙሉ ማሟላቱን የሚያሳይ ነው ብሏል።

ኢሰመኮ የደረጃ “A” እውቅና (ወይም አንደኛ ደረጃ እውቅና -“A” Status Accreditation) እንዲያገኝ አስተዋጽዖ ላደረጉ ባለድርሻ አካላትም ምስጋናውን አቀርቧል።

የዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) የእውቅና ገምጋሚ ንዑስ ኮሚቴ እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 8 እስከ ጥቅምት 19 ቀን 2021 ባደረገው ጉባዔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጥምረቱ የተከናወነውን ጠንካራ የግምገማ ሂደት ማለፉን ተከትሎ፣ ለኮሚሽኑ የደረጃ “A” እውቅና (አንደኛ ደረጃ እውቅና - “A” Status Accreditation) መስጠቱን በትናንትናው ዕለት ነው ያስታወቀው።

ጥምረቱ ኮሚሽኑ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም የሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ እና ለማስፋፋት እየተጫወተ ያለውን ሚና ያደነቀ ሲሆን በተለይም እ.ኤ.አ. በኅዳር ወር 2013 በጥምረቱ ተለይተው የነበሩ ጉድለቶችንም ለማስተካከል ያደረገውን ጥረት አመስግኗል።

የዓለም አቀፉ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት (GANHRI) 118 ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የሆኑ አባላት ህብረት ሲሆን ከፓሪስ ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መመስረትን እና መጠናከርን የሚያበረታታ ነው።

በ1993 የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ያጸደቀውና በአጭሩ የፓሪስ መርሆዎች ተብሎ የሚጠራው የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መርሆች (Principles Relating to the Status of National Institutions) የተቋማቱን ተዓማኒነትና ብቃት ለመገምገም የሚያገለግል ሰነድ ሲሆን፣ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተቋማት በሕግ፣ በአሰራር፣ በአባልነት፣ በፖሊሲ እንዲሁም በፋይናንስ ገለልተኛ እና ከጣልቃ ገብነት ነጻ እንዲሆኑ ይደነግጋል።

የፓሪስ መርሆች መገምገሚያ መስፈርቶች፡- የተቋማቱ ኃላፊነት እና ሥልጣን ስፋት፣ የሰው ሃብታቸውን ብዝኃነት፣ የተግባራትና እና የገንዘብ አቅም፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ትብብር ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ (UNOHCHR) የጥምረቱ (GANHRI) ጽሕፈት ቤት ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፣ የጥምረቱ የእውቅና ገምጋሚ ንዑስ ኮሚቴ (Sub-Committee on Accreditation- SCA) ደግሞ በዚሁ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት እየታገዘ የእውቅና ጉዳዮችን ገምግሞ ምክረ-ሃሳቦችን የሚያቀርብ ገለልተኛ አካል ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ድርጅታዊ አቋሙን እና አሰራሩን ለማሻሻል ያስቻሉ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ሲያደርግ መቆየቱን ኮሚሽነር ዶር ዳንኤል በቀለ የገለፁ ሲሆን የተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ የተቋሙን የአሰራር እና የበጀት አስተዳደር ነፃነት ከማረጋገጡም ባሻገር በምርጫ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል ስራዎችን እንዲያከናውን እንዲሁም ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የእስር ቦታዎችን ለመጎብኘት በማስቻሉ የኮሚሽኑን ሥልጣን ከማጠናከር አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

አክለውም ኮሚሽኑ ያገኘው እውቅና ትልቅ እመርታ መሆኑን አመልክተው፣ ተቋሙን በማሻሻል ሂደት ውስጥ በመሳተፍ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም የኮሚሽኑን ተልዕኮ በማስፈጸም ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ላሉት የኮሚሽኑ ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ “

[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]


3 min read

Published

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now