የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የዲጂታልና ውጪ ሚዲያዎች ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢልለኔ በመግለጫቸው እንዳሉት ሕወሓት ወረራ በፈጸመባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩም አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚሹ ገልጸዋል።
ቃል አቀባይዋ ሕወሓት ወረራ ፈጸሞባቸው በነበሩት አካባቢዎች የጅምላ ግድያዎችን ፈፅሟል ያሉ ሲሆን በተለይም በአማራ ክልል አንጾኪያ እና ጋሸና የጅምላ መቃብሮች መገኘቱን አስረድተዋል። ከዚህ ባለፈም በአፋርና አማራ ክልሎች ሴቶችን መድፈሩን እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ማድረሱንም የጠቆሙት ኃላፊዋ ወንጀሎቹን የሚያጣራ እና ማስረጃ የሚሰበስብ አጣሪ ቡድን ወደ ቦታው መላኩን አስታውቀዋል።
ኃላፊዋ በመግለጫቸው የሰብአዊ ድጋፍ የሚሰጡ አውሮፕላኖች ወደ መቀሌ በመብረር ላይ መሆናቸውን ያነሱ ሲሆን በቅርቡም 203 ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች መቀሌ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰብአዊ እርዳታን በማድረስ ረገድ ትኩረቱን ወደ ትግራይ ክልል ብቻ ማድረጉን የተናገሩት ቢልለኔ በአፋር እና አማራ ክልሎች ውስጥ የህወሓት ቡድን የፈፀማቸውን ወንጀሎችንም ችላ ማለቱ ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው ነው ሲሉ ወቅሰዋል። እንደ አብነት ሲጠቅሱም ወደ ትግራይ ለሰብአዊ እርዳታ ተልከው ህወሓት ታጣቂዎቹን ለማመላለስ እየተጠቀመባቸው የሚገኙ 900 ተሽከርካሪዎች በሄዱበት ሲቀሩ እንዳልሰሙ በቸልታ አይተዋል ብለዋል፡፡
በሌላ መልኩ ከ5 ሺህ በላይ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች የጫኑ 30 የጭነት መኪኖች በሰሜን ወሎ አካባቢዎች ማለትም ለጋሼና እና ላሊበላ ዙሪያ ተጓጉዟል ያሉት ቢልለኔ በአፋር ክልል 400 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከ17 ወረዳዎች መፈናቀላቸውንና ከ 64 ሺህ ኩንታል በላይ ምግብ ለእነዚህ ተፈናቃዮች መድረሱንም አውስተዋል።
ቢልለኔ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው የሕወኃት ኃይል በኢትዮጵያ ጥምር ጦር እየተደመሰሰ እና ታጣቂዎቹም በመንግስታቸው የቀረበውን አማራጭ በመጠቀም እጅ እየሰጡ ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጓዳኝም መንግስት በአሁኑ ወቅት ለተፈናቃይ ወገኖች የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ድጋፉ ማድረሱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
(ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ)

