የኢትዮጵያ መንግሥት እሥረኞችን በምሕረት መፍታቱን አስታወቀ።
እንዲፈቱ የተወሰነላቸው እሥረኞም "ቀደም ሲል በተፈጸመ ጥፋትና በቅርቡ ከተፈጠረው ጦርነት ጋር በተያያዘ የታሠሩትን" የሚያካትት ነው ሲል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገልጧል።
አያይዞም "መንግሥት ይሄንን ውሳኔ ሲወስን ዓላማው የኢትዮጵያን ችግሮች ሰላማዊ በሆነ፣ ከእልክና ከመጠፋፋት በራቀ ሁኔታ፣ በሀገራዊ ምክክር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንገድ ለመክፈት ነው። በተጨማሪም የሕዝብን ጥያቄዎች ከግምት በማስገባትና ምንጊዜም ለሰላማዊ ፖለቲካ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ነው" ብሏል።
ከእሥር የተለቀቁትም "አገራቸውንና ሕዝባቸዉን ይክሳሉ ብሎ መንግሥት ያምናል" ያለ ሲሆን "በሂደቱ የተጎዱ ወገኖች እንደሚኖሩ መንግሥት ያምናል። የእነዚህ ተጎጂ ዜጎች ቁስል በሽግግር ፍትሕ የሚካስ ይሆናል። እነዚህ ተጎጂ ዜጎች ሕመማቸው ለኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ ሸክማቸውን መንግሥትና ሕዝብ በጋራ እንሸከምላቸዋለን። ከእሥር የተፈቱ ወገኖችም ጭምር የተጎጂዎችን ሸክም የመሸከም ዕዳ አለባቸው" በማለት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመንግሥትን አቋም አንፀባርቋል።
በዚህም መሠረት ታህሳስ 29, 2014፤
1. አቶ ስብሐት ነጋ
2. ወሮ ቅዱሳን ነጋ
3. አቶ ዓባይ ወልዱ
4. አቶ አባዲ ዘሙ
5. ወሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር
6.ወ/ሮ ኪሮስ ሐጎስ
7. አቶ ጁሐር መሐመድና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ
8. አቶ እስክንድር ነጋና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ ከእስር እንዲፈቱ ተወስኗል

