የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን መገናኛ ባለሙያዎች ማኅበር ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተጣሩ ዘገባዎችን እንዲያስተላልፉ አሳሰበ

*** ማኅበሩ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም የየትኛውም መገናኛ ብዙኅን ዘጋቢዎች ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙና በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው እውነተኛ መረጃ ለሕዝብ ማቅረብ እንዲችሉ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስቧል።

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

የተወሰኑ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተዛቡ፣ ትክክለኛ የጋዜጠኝነት መርህን ያልተከተሉ፣ የአገር ሉዓላዊነትና የህዝቦችን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ብሎም የፖለቲካዊ ውግንና ያላቸውን ዘገባዎች ማሰራጨታቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር አጥብቆ ኮንኗል።

ማህበሩ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ የሰሩትን ዘገባ አስመልክቶ በአማርኛና እንግሊዝኛ መግለጫ አውጥቷል።

በዚህ መግለጫው ሰሞኑን አዲስ አበባን እና ዙሪያዋን በተመለከተ የተሰራጩ ዘገባዎችን ትክክለኛነትና ሚዛናዊነት ለማጣራት ጥረት ማድረጉን ገልጿል።

ለዘገባ ከተንቀሳቀሱና በየአካባቢው ከሚኖሩ አባሎቹ ብሎም ከነዋሪዎች ባገኘነው መረጃ መሰረት እስካሁን ድረስ አዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙት አካባቢዎች ሁሉ በተለመደው እንቅስቃሴያቸው ላይ ይገኛሉ ብሏል።

ማህበሩ ከሰሞኑ ሲኤንኤንና መሰል ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች የተዛቡ እና ፖለቲካዊ ውግንና ያላቸውን ዘገባዎች ማሰራጨታቸውን አጥብቆ የኮነነ ሲሆን በእንደዚህ ያሉ ሙያዊ መርሆን ባልተከተሉ ዘገባዎች እየተሳተፉ ያሉ ጋዜጠኞች ጋዜጠኝነታቸውን በሙያዊ አስተምህሮው መሰረት እንዲፈፅሙ ጠይቋል።

በተጨማሪ መቀመጫቸውን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ያደረጉና ስለኢትዮጵያ የሚዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች ከእንደዚህ አይነት አዘጋገብ እንዲወጡ አጥብቆ አሳስቧል።

 የኢትዮጵያ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም የየትኛውም መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎች ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙና በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው እውነተኛ መረጃ ለህዝብ ማቅረብ እንዲችሉ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስቧል።

 የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም ፈጣን፣ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ መክሯል።

 [ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]


1 min read

Published

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now