የአማራ ክልል ምክር ቤት ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት እንዲዘጋ የአስቸኳይ ጊዜ አወጀ

*** የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸዉ ተቋማት ዉጭ በሁሉም ከተሞች ከምሽቱ 2፡00 በኋላ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይቻልም ተደንግጓል።

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

የአማራ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት ጥቅምት 21 2014 ባካሔደው 6ኛው ዙር 1ኛ ዓመት 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባ "በተጨባጭ እየገጠመን ያለዉን የሕልዉና አደጋ ለመቀልበስ በመደበኛዉ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ብቻ ማሸነፍ የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ የአስቸካይ ጥሪ ዉሳኔዎች አስተላልፏል" ሲል ባለ ዘጠኝ ነጥብ ውሳኒዎቹን ባወጣው መግለጫ ገልጧል።

 ውሳኔዎቹም፤ ማንኛዉም የመንግስት ተቋም መደበኛ አገልግሎቱን አቋርጦ በጀቱን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የገጠመንን የህልዉና ዘመቻ ለመቀልበስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንዲረባረብ ተወስኗል፣ ሁሉም የመንግስት ተሸከርካሪ ወደ አንድ ማዕከል በማሰባሰብ ለሕልዉናዉ ዘመቻ አገልግሎት እንዲዉል ይደረጋል፣ የግል ተሸከርካሪ ባለቤቶች ለሕልዉና ዘመቻዉ ስኬት ሲባል በተፈለገ ጊዜ ሁሉ ተሸከርካሪዎቻቸውን በመስጠት ኃላፊነታቸዉን እንዲወጡ፣ አመራሮች ሕዝብን አደራጅተው ብኝባር ቀደምትነት እንዲዘምቱ፣ የመንግሥትና የግል የጦር መሳሪያዎች ለዘመቻው እንዲውሉና ሕዝባዊ ተሳትፎዎችም በሎጂስቲክና ፀጥታ ተግባራት እንዲሰማሩና የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸዉ ተቋማት ዉጭ በሁሉም ከተሞች ከምሽቱ 2፡00 በኋላ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይቻል አስታውቋል።

በሌላም በኩል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በሚገጥመን ፈታና ሳንረበሽ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና ከተጫወትን ፈተናችን የሚወገድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። በተቃራኒው ተግባሩን ትተን የምንተይቅ ብቻ ከሆንን የድላችን ዕድሜ ይዘገያል። ህገርን የመከላከል ኃላፊነት የጥቂቶች ሳይሆን የሁላችንም ነው" ብለዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለም የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ኮምቦልቻ በድርጅታቸው ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆኑን ገልጠዋል። ሆኖም በመንግሥት በኩል የተሰጠ ማረጋገጫ የለም።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ሳምንቱን ሲያካሂድ ከቆየው የአየር ድብደባ ጋር ተያይዞ እሑድ ዕለት ማይ ፀምሪ ያሉ የሕወሓት ማሰልጠኛ ጣቢያዎችና ዴፖዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ተናግረዋል።   

የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ማይ ፀምሪ ሆስፒታል አጠገብ የአየር ጥቃት ተፈጽሟል ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል። አያይዘውም በመንግሥት በኩል አድዋ ላይ ተፈፀመ የተባለው የአየር ጥቃት ያደረሰው ጉዳት እንደሌለም ገልጠዋል። 

 


2 min read

Published

By Stringer Report


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now