ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ትናንት ጃኑዋሪ 10 በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፅ የስልክ ውይይት አደረጉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይም መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ወቅት አገራቱ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ገንቢ ተሳትፎ ለማድረግ እንደመከሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
በሌላም በኩል ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሔደ ስላለው ግጭት፣ ሰላምና ዕርቅን ለማስፈን ስላሉት መልካም አጋጣሚዎች ማንሳታቸውን ገልጧል።
አያይዞም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በርካታ የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታታቸውን በመልካም ጎኑ ማንሳታቸውን፣ የተኩስ አቁም ድርድር ለማድረግ የሚፋጠንበትን መንገድ፣ በመላው ኢትዮጵያ የረድኤት አቅርቦት ስለሚከናወንበት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳቢያ የታገቱትን ኢትዮዖጵያውያኖችን አካትቶ ሁሉንም አሳሳቢ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የደረሱባቸውን ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ መነጋገራቸውን ጠቅሷል።
የዋይት ሐውስ መግለጫ አክሎም፤ ፕሬዚደንት ባይደን እየተካሔዱ ባሉት የአየር ጥቃቶች ሳቢያ እየደረሱ ያሉትን የሰላማዊ ሰዎች ለጉዳትና ስቃይ መዳረግ እንዳነሱና ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያውያን ግጭቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ከአፍሪካ ኅብረትና ከቀጠናው ሽርካዎች ጋር አብራ እንደምትሠራ ያረጋገጡ መሆኑን አስታውቋል።
እንዲሁም፤ ሁለቱም መሪዎች የዩናይትድ ስቴትስና የኢትዮጵያ ግንኙነቶችን ጠቀሜታ ሁነኛ መሆኑን፣ መጠነ ሰፊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትብብሮቻቸውን ለማጠንከር አመቺ ሁኔታዎች መኖራቸውንና ግጭቱን ለመክላት ተጨባጭ እርምጃዎች እንደሚያሹ አበክረው ማንሳታቸውን አስፍሯል።
የሁለቱን አገራት መሪዎች ንግግር አስመልክቶ በሕወሓት በኩል የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ጃኑዋሪ 8 በኢትዮጵያ አየር ኃይል በተሰነዘሩ የአየር ጥቃቶች ሳቢያ የ56 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ከ100 በላይ ለመቁሰል አደጋ መዳረግ ን ጃኑዋሪ 9 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አክሎም፤ በኤርትራ ጦር ሽራሮ አካባቢ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጧል።

