በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የዩኒቨርሲቲ ትምህርት በመቋረጡ የተነሳ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተለየዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲቀጥሉ ትምህርት ሚኒስቴር መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ በአክሱም ዩኒቨርሲቲና በመቀሌ ዩኒቨርሰቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ መሃል 873 ተማሪዎችን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራርና አሉሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሌው በላይነህ ገልፀዋል፡፡

ከእነዚህ መካከልም ለምርቃት የሚያበቃቸውን የመጨረሻ ዓመት ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ 223 ወንድና 164 ሴት በድምሩ 417 ተማሪዎች የመጨረሻ ሴሚስተር ትምህርታቸውን አጠናቀው ቅዳሜ ሰኔ 4 በይፋ የማጠናቀቂያ ዕውቅና ስነ ስርዓት ተዘጋጅቶላቸዋል”ብለዋል፡፡ ዶ/ር ብርሌው “ዛሬ ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ተማሪዎች ቀደም ሲማሩባቸው ከነበሩ ሶስቱ ዩኒቨርሲቲዎች ኦፊሺያል ዲግሪቸውን እስኪያገኙ ድረስ ጊዜያዊ የማጠናቀቂያ ማስረጃ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅቶላቸዋል” ብለዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ በበኩላቸው “ በትግራይ ክልል በሚገኙ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የነበሩና በተፈጠረው ግጭት የተነሳ ትምህርታቸውን መቀጠል ያልቻሉ የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲያችን በአደራ ተቀብሎ ለመጀመሪያ ዲግሪ የሚያበቃቸውን ኮርስ እንዲያጠናቅቁ አድርጓል፤ በዚህም ዩኒቨርሲቲያችን ይህንን በማድረግ በሀገርና ህዝብ የተጣለበትን ኃላፊነት በሚገባ ተወጥቷል” ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ተማሪዎቹን ፈተናዎች ያልበገሯቸው ጀግኖች ሲሉ ያሞኳሹ ሲሆን በ1982/83ዓ.ም በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት የደርግ መንግስትን ለመጣል ሲደረግ በነበረው ጦርነት እርሳቸውም ትምህርታቸውን ለማቋረጥና በሌላ ዩኒቨርሲቲ ለማጠናቀቅ መገደዳቸውን በማውሳት ለተማሪዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
ዶ/ር ፍሬው ለተማሪዎቹ እንዳሉት በዚያ ጦርነት ወቅት በአስመራ ዩኒቨርሲቲ ግቢ አናት ላይ የጦር ሄሊኮፕተሮች በየደቂቃው እያንዣበቡ በሰላም እጦት ይቸገሩ እንደነበር አውስተው “ እናንተ በምን ሁኔታ ውስጥ ቆይታችሁ ወደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ እንደመጣችሁና ዛሬ ለማጠናቀቅ እንደበቃችሁ በውል ስለምረዳ ሊነጋ ሲል ይጨልማል እንደሚባለው ከዚህ በኋላ እናንተም ከጨለማው ወጥታችሁ ወደ ብርሀን ጉዞ ጀምራችኋል - እንኳን ለዚህ አበቃችሁ” ብለዋል፡፡

ፕሬዝደንቱ አክለውም “የጦርነትን አውዳሚነት ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተምሯል፤ በተለይ ጀርመንና ጃፓን ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ናቸው” ያሉ ሲሆን “እናንተም በዚህ ወቅት ህዝባችንና ፖለቲከኞቻችን የጠፋባቸውን ውል ለማቅናት የመፍትሔው አካል ሁኑ፤ ጥበብን የምትሹና የመፍትሄ አካል መሆን ባትችሉ እንኳን እንቅፋት ባለመሆን ለሀገራችሁ ውለታ ዋሉ” ሲሉ አደራ ብለዋል፡፡
የመጨረሻ ሴሚስተር ትምህርታቸውን ካጠናቀቁትና ዛሬ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የእውቅና ስነ ስርዓት የተገኘችው ምንታምር አስማረ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሲቪክስ ኢዱኬሽን የመጨረሻ ዓመት ተማሪ የነበረች ሲሆን “መከላከያ መቀሌን ለቅቆ ሲወጣ በተፈጠረው ሁኔታ ትምህርታችንን መከታተል አልቻልንም፡፡ ብዙ ጓደኞቼ በትምህርት ሚኒስቴርና በቀይ መስቀል አማካኝነት እንዲወጡ የተደረገ ቢሆንም እኔ ግን በእግሬ ተጉዤ ነው ከትግራይ ክልል የወጣሁት” ስትል የወቅቱን ሁኔታ ለኤስቢኤስ ዘጋቢ አውስታለች፡፡
ምንታምር እንዳለችው “በሰቆጣ በኩል አቋርጬ ወጣሁ፤ የዋግኽምራ ህዝብ ያለውን አካፍሎ ወደ ቤተሰቦቼ በሰላም ሸኝቶኝ ያቋረጥኩትን ትምህርት ዛሬ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጠናቅቄያለሁ፤ በዚህም በጣም ደስ ብሎኛል፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ላደረገልን ነገር ሁሉ አመሰግናለሁ” ብላለች፡፡
ትናንት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዊዝደም አዳራሽ “የትምህርት ማጠናቀቂያ ዕውቅና ስነ ስርዓት” የተዘጋጀላቸው 417ቱ ተማሪዎች በ7 የተለየዩ አካዳሚዎች ውስጥ ባሉ የትምህርት መስኮች ሲማሩ መቆየታቸውን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡
( ደመቀ ከበደ - ከባሕር ዳር )

