የዩናይትድ ስቴትስ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ እና ምክትል ልዩ ልዑክ ፓይተን ኖፍ ዛሬ ኤፕሪል 13 አዲስ አበባ ይገባሉ።
ልዑካኑ ከኢትዮጵያ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የረድኤት ድርጅቶች ተወካዮችና የዲፕሎማሲ ሽርካዎች ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ።
የጉብኝታቸው ተልዕኮም ዩናይትድ ስቴትስ ግጭቶች እንዲገቱ ፣ ገደብ አልባ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲኖር፣ በሁሉም ተዋናዮች ዘንድ ግልፅነተ የተመላበት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራዎች እንዲካሔዱና ኢትዮጵያ ላለው ግጭት በድርድር ዕልባት ለማበጀት በምታደርጋቸውን ጥረቶች መቀጠል እንደሆነ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በወርኃ ጃኑዋሪ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ልዑክ ሆነው የተመደቡት የቀድሞው በቱርክና ሊባኖስ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ለጊዜው ይህ ነው ባልተባለ ይፋዊ ምክንያት የሥራ ኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ፎሪን ፖሊሲ መፅሔት ዲፕሎማሲያዊ ምንጮን ጠቅሶ ገልጧል።
በምትካቸውም በጊዜያዊነት ምክትላቸው ፓይተን ኖፍ በተጠባባቂነት የሥራ ኃላፊነቱን ተቀብለው እንደሚቀጥሉ ተጠቁማል።

