ዛሬ ከኢትዮጵያ ታላላቅ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሁለተኛው ትውልድ ተርታ የሚመደብ ፤ ግን በተግባራቱ ከግንባር ቀደሞቹ የፊት ረድፍ ላይ የሚሰለፈው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግማሽ ክፍለዘመንን በተሻገረ ዕድሜው ዕልፎችን ቀለም አስጨብጦ፤ ህልቆ መሳፍርትን ለአገርና ወገን አሰለሳይነት አፍርቶ አንቱታን መገለጫው አድርጓል፡፡ በሁለት ተቋማት ውህደት ዩኒቨርሲቲ የሆነው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በውስጡ 5 ኮሌጆችን፣ 4 ኢንስቲትዩቶችን፣ 2 ፋካልቲዎችን እና 2 ትምህርት ቤቶችን በድምሩ 15 አካዳሚዎችን አቅፎ ይዟል።
በጣት የሚቆጠሩ የትምህርት መስኮችን በተለምዶ ፖሊ እና ፔዳ በተሰኙ የኢንጂነሪንግና የ”ኢዱኬሽን” መስኮች ያስተምር የነበረው ተቋም ዛሬ 112 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 187 የሁለተኛ ዲግሪ፣ 89 የሦስተኛ ዲግሪ፣ 12 ስፔሻሊቲ፣ 3 ሰብ ስፔሻሊቲና 6 ሰርተፊኬት ደረጃዎችን በድምሩ በ409 መርኃግብሮች ከ40 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል፡፡
ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ጋር መሳ ለመሳ ለባሕር ዳር የከተማነት ዝማኔ ጉልሕ ድርሻ ያበረከተው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከከተማዋ ስሟን ብቻ ሳይሆን ውበቷንም ወርሶ ካምፓሶቹን ሁሉ በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫ እየከፈተ ዝምንናዋን ከጎን ስፋት፣ ከውስጥ ዕድገት ጋር እያሰናሰለ አብሯት እየተጓዘ ነው፡፡
ለሀገርና ለአጠቃላይ የከፍተኛ ትምህርት እድገት ከሚያበረክተው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አስተዋፅኦ በመለስ ለባሕር ዳር ከተማ በምርምርና ማሕበረሰብ ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በቴክኖሎጂ ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን እያበረከተ ለመሆኑ ከተማዋን ዘወር ዘወር ብሎ የተመለከተ፣ የጣና ደሴቶችን ለማየት በታንኳ የተንሳፈፈና በዓባይ ውሃ ፖለቲካ ንባብ የተለከፈ ሁሉ መረዳት የሚቸግረው አይደለም፡፡
ለዚህም ይመስላል ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመቱን ሊያከብር ጉድ ጉድ መጀመሩን በተመለከተ ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው መግለጫ ላይ የዩኒቨርሰቲው አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባም መድረኩ ላይ ከፊት ለፊታችን አብረው የተሰየሙት፡፡

በዚህ የ60ኛ ዓመት ልዩ አከባበር ቅድመ ዝግጅት መግለጫ ወቅት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዳሉት “ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ” በሚል መሪ ቃል የሚታወቀው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከሚገኙት 51 ዩኒቨርሲቲዎች ግዙፍና ቀዳሚ ከሆኑት መሀል አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ባሳለፋቸው ረጂም ዓመታት እንደ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ፣ ያሳካቸውን ግቦችና ወደፊት ያቀዳቸውን ውጥኖች ለባለድርሻዎች ሁሉ ለማስቃኘት የሚያስችል የአንድ ዓመት የበዓል አከባበር ታቅዷል፡፡
“የዩኒቨርሲቲያችን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መስከረም 2015ዓ.ም 50 ዓመት የሚሞላውን የቀድሞውን ፔዳጎጂ አካዳሚ ምስረታ ምክንያት በማድረግ ተጀምሮ ለዩኒቨርሲቲው ውልደት እርሾ በሆነውና 60ኛ ዓመቱን በሚደፍነው የቀድሞው ፖሊቴክኒክ ኢኒስቲትዩት ምስረታ ቀን ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል” ሲሉ ም/ፕሬዝደንቱ ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዘውዱ ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት የአንድ ዓመቱ ስነ ስርዓት ሁለንተናዊ የዩኒቨርሰቲውን ነባራዊ ሁኔታ በሚያሳዩ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚከወን ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ዘውዱ ገለፃ፤ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ፈጠራ ስራዎች እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ብሎም የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያሳዩ አውደ ርዕዮችን በተለያዩ ስፍራዎች መከወን አንደኛው የበዓሉ አንኳር ሲሆን በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን የሚሳተፉባቸው የተለያዩ የምክክር መድረኮችም ይከናወናሉ፡፡

በተጨማሪም የጥናትና ምርምር ጉባኤዎች፣ የቴክኖሎጂና የኪነ ጥበብ ፈጣራ ውድድሮች፣ እንዲሁም የደም ልገሳና ችግኝ ተከላን የመሳሰሉ የዩኒቨርሲቲውና የባሕር ዳር ከተማ ማህበረሰብ ያሳተፉ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ክንውንም የመርኃ ግብሩ አካሎች ናቸው፡፡ ለዩኒቨርሲቲው ዛሬ ላለበት ግዝፈት አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትና ግለሰቦች የምስጋናና ሽልማት ስነ ስርዓትም የሚደረግ መሆኑን ዶ/ር ዘውዱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በ”መንግስት ሹመት ሳይሆን” በዩኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል በተደረገ ውድድር የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንትነትን ኃላፊነት በመውሰድ ፈረ ቀዳጅ የሆኑትና አሁንም ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዝደንትነት የሚመሩት ዶ/ር ፍሬው ተገኝም በጋዜጣዊ መግለጫው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በርካታ አካዳሚያዊና ችግር ፈቺ የምርምር ስኬቶችን አሉን ያሉት ዶ/ር ፍሬው ለአንድ ዓመት ያህል የዩኒቨርሲቲውን የት መጣዊነትና ሀገራዊ አስተዋፅኦ ከወደፊት ፍኖቱ ጋር አሰናስሎ ለማክበር የተወጠነበት ዋና ምክንያት “ዩኒቨርሲቲው በተጓዘባቸው ስድስት አስርት ዓመታት ያስመዘገባቸውን ውጤቶች የተቋሙና የውጪው ማህበረሰብ ይበልጥ እንዲያውቃቸውና ለቀጣዩ የዩኒቨርሲቲው ራዕይ መሳካት በጋራ እንዲነሳ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ ነው” ብለዋል፡፡

በሌላ መልኩም “ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን ዕውቅና ለመስጠትና ለወደፊቱም ለተቋሙ ዕድገት የሚበጁ ጉዳዮች ላይ ምክክርና እገዛቸውን እንዲቀጥሉ ለማስቻል ጭምርም ነው ብለዋል፡፡ አክለውም በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፋዊ ክሱትነት ተወዳዳሪነቱንም ለማጉላት ዓላማ አድርገው ክብረ በዓሉን ለማክበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በጣና፣ ዓባይና ዘንባባዋ የብዙዎችን ቀልብ የምታማልለው ባሕር ዳር ከተማ፤ ከዩኒቨርሲቲው ያገኘችውን ጠቀሜታ በተመለከተ ንግግር ያደረጉት የከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳሕሉ ዩኒቨርሲቲው በከተማዋ ውስጥ ያለ ከተማ ነው ብለዋል፡፡ ከንቲባው “በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ60 ዓመት ጉዞ የተጠቀምነው ብዙ ነው፤ የከተማዋ የዕድገት ጉዞና የተመዘገበው ስኬት ከዩኒቨርሲቲው ጉዞ ጋር የተቆራኘ ነው”ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ከንቲባው አክለውም “በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ክፍተቶችን እየለየ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ የሩቁን ታሪክ ትተን ኮቪድ 19 በተከሰተ ወቅት በመከላከልና ለማህበረሰቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የላቀ ሚና ተጫውቷል” ብለዋል፡፡ የስራ ዕድልን ጨምሮ ከተማዋና የከተማው ህዝብ ከዩኒቨርሲቲው የሚጠብቃቸውን የተለያዩ አበርክቶዎች ሁሉ እየፈጸመ ነው ያሉት ዶ/ር ድረስ ለከተማዋ ዘመናዊነት የሚረዱ ፋይዳ ያላቸው ስራዎችንም ሰርቷል ብለዋል፡፡ “የባሕር ዳር ከተማ የ30 ዓመት ስትራቴጂክ ፍኖተ ካርታ በዩኒቨርሲቲው ነው የተዘጋጀው፤ ይህ ፍኖተ ካርታ የቱሪስት መዳረሻዋን ውብ ከተማ የሚመጥንና ወቅቱን የጠበቀ ነው” ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲውን የተለያዩ ክንውኖችና የምርምር ውጤቶች በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርበው አመራሮቹ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ በሚል መሪቃል ራሱን የሚገልፀውና ከዓባይ ጉያ ስር የተመሰረተው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለዓባይ ውሃ ፖለቲካ ረብ ያላቸውን ምን ምን ስራዎች ሰርቷል የሚል ጥያቄ ከኤስ ቢ ኤስ ዘጋቢ የቀረበላቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ምላሽ ሰጥተዋል፤ ዶ/ር ፍሬው እንዳብራሩት ዩኒቨርሲቲው በዓባይ ውሃ ጉዳይ በርካታ የምርምር ተግባራትና የመማር ማስተማር ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
“ከአምስቱ የምርምር ተቋሞቻችን ውስጥ ጥቁር ዓባይ የውሃ ኢኒስቲትዩት ዋናው ነው፤ ይህ ተቋም ከአስር ዓመት በላይም ሆኖታል፡፡ የውሃ ሀብት ኢንጂነሪንግን ጨምሮ በርካታ በውሃ ዙሪያ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን እያስተማርን ነው፡፡ በዚህ ኢንስቲትዩታችን አማካኝነት በሚታተሙ ውሀ ተኮር የምርምር ህትመቶች ረገድ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዎች ነን” ብለዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ለአብነት የህዳሴ ግድቡን ዕድሜ ለመጨመር እስከ ሶስት እጥፍ ማራዘም የሚያስችል የምርምር ስራ ለፖሊሲ አውጪዎችና የውሳኔ አካላት ግብአት እንዲሆን ማበርከታቸውን ገልፀዋል፡፡
በዓባይ ውሃ ጉዳይ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ በተለይም ከሱዳን 12 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጋራ ስምምነት በመመስረት እየሰራን ነው ያሉት ዶ/ር ፍሬው በደቡብ ሱዳንም የውሃ ትምህርት ፕሮግራም መክፈታቸውን ገልፀዋል፡፡ በአካባቢ ጥበቃ ረገድም በተለይም በጮቄና ብር አዳማ በተባሉ የዓባይ ወንዝ የውሃ ጋኖች ዙሪያ ጠንካራ የተፈጥሮ ጥበቃ ሰራዎችን እየሰራን ነው የሚሉት ፕሬዝደንቱ የጣና ጠንቅ በሆነው እምቦጭ አረም ዙሪያም ጉልህ ሚና ለመወጣት ዩኒቨርሲቲያቸው ጥረት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ “ጣና ሳይኖር ዓባይ አይኖርም፤ ስለዚህ የእምቦጭ አረምን ስጋትነት ለመቀነስ የእምቦጭን መስፋፋት ምክንያትና የጉዳት መጠን የተመለከቱ ብሎም ከአረሙ ማዳበሪያ፣ መኖ፣ ሃይል ማመንጫና የተለያዩ ቁሳቁሶችን እንዴት ማምረት እንደሚቻል የሚያሳዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሰርተናል” ሲሉ የሰጡትን ትኩረት አብራርተዋል፡፡
እንደ አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋምነቱ ዩኒቨርሲቲው በተለይ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ረገድ ምን ስራዎችን ሰርቷል የሚል ጥያቄ ያቀረበንላቸው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጠንካራ የግንኙነት ስትራቴጂ እየተከተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፤ ለጉዳዩ የሰጡትን ትኩረት “በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ባልተለመደ ሁኔታ የኢንፎርሜሽንና የስትራቴጂክ ግንኙነትን የሚሰራ ምክትል ፕሬዚደንት” ያለው ተቋም መሆኑን በአስረጂነት ጠቅሰዋል፡፡
ም/ፕሬዝደንቱ ዶ/ር ዘውዱ “ከ180 በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት መስርተናል፤ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ኔትወርኮችን አባል ሆነናል፡፡ በውሃ፣ በኢነርጂ፣ በህክምና፣ በግብርናና መሰል መስኮች ልህቀት ያለው ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከስምንቱ የኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ዩኒቨርሲቲያችን” ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዘውዱ አክለውም ከቤልጅዬም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለአስር ዓመታት የቆየና ከ18 በላይ የትምህርት ክፍሎችን ያካተተ የአቅም ግንባታ ስራዎች ግንኙነት አለን ብለዋል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱም ሆነ የቆመላቸው ተልዕኮዎቹ ስኬታማ እንዲሆኑ የቀድሞ ምሩቃንን በተለየ ሁኔታ የማሳተፍ ስራዎች እንደሚሰሩ የገለፁት ዶ/ር ዘውዱ ለዚህ ስኬትም ከ120 በላይ በሆኑና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ፕሮፌሰሮችን በማካተት በአካባቢ ጥበቃና ግብርና ስራዎች ላይ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝም ለቀድሞ ምሩቃን ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን የቀለም ትምህርት ቤታቸውን በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም የሚገኙ ፍሬዎቹ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉለት አደራ ብለዋል፡፡
(ደመቀ ከበደ - ባሕር ዳር)

