ለሁለት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ ሲካሔድ የነበረው የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ስብሰባ ነሐሴ 6/2012 ተጠናቅቋል።
የስብሰባውን ሂደትና ክንውኖች አስመልክቶ የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር መግለጫ ሰጥተዋል።
በዋነኛነት በፓርቲው ጉባኤ ውይይትና ግምገማ የተካሔደባቸውንና ውሳኔዎች የተላለፉባቸውን ጉዳዮች ሲገልጡም፤
- ያለፉት የሁለት ዓመት ተኩል የለውጥ ጉዞና ፈተናዎች
- በክልሉና በአገሪቱ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የተከናወኑ ተግባራት
- ወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች
- የብልጽግና ፓርቲ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ሥራዎች
- የክረምት የግብርና ሥራዎች
- ባለፈው ሰኔ 22 ቀን በአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በብሔርና ሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችና ማፈናቀሎች በጥልቀት ተገምግመው የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው አቅጣጫ መቀመጡን አመላክተዋል።
አያይዘውም፤ የአማራ ክልልን ከግጭትና ሥጋት ለመታደግ በሕዝብና በመንግሥት የተከናወኑት ተግባራት አበረታች ስለሆኑ ክንውኖቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ብሔርና ሃይማኖትን ለይተው የተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሕይወቶችን ለሕልፈትና መፈናቀል መዳረጉንና ንብረቶችን ለውድመት የማብቃቱ ሁነት በትህነግና ኦነግ ሸኔ ድጋፍ እንደሆነ መገምገሙን አቶ አገኘሁ ገልጠዋል።
ድርጊቱን የፈጸሙ አጥፊዎች ወደ ሕግ እንዲቀርቡና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድባቸው በቁርጠኝነት ለመሥራት ከግብቦሽ ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
አቶ ተሻገር አክለውም፤ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስለ ብልጽግና ፓርቲ የተናገሩትና ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ሐሳብ የተሳሳተና የፓርቲውን አቋም የማይገልጽ የግለሰብ አቋም ስለመሆኑ ግንዛቤ መወሰዱንና ያነሱት ሐሳብም በብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በኩል በጥልቀት ተገምግሞ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ ማለፉን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ የኦሮሞና የአማራ ህዝብን ወንድማማችነት መበጠስ እንደማይቻልና "እኛ ኖርንም አልኖርንም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩና ወንድማማችነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል" እንዲሁም፤ "አማራን ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ትህነግ ሊነጥለው አይችልም" ሲሉም አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

