ከሰሞኑ በተለያዩ ዓለም አቀፍና የሀገር ቤት የዜና ምንጮች “ከሕወኃት ጋር ድርድር እየተካሄደ” ስለመሆኑ የሚነገሩ መረጃዎችን በተመለከተ መንግስት በግልፅ እንዲያሳውቅ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ያቀረቡበትና የጠቅላይ ሚኒስተሩ ምላሽ ትኩረት ስቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው “ሕዝብ ሳያውቀው የሚደረግ ድርድር የለም። በይፋ የታወቀ አጥኚ ኮሚቴ ተቋቁሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት እየተመራ ሲሆን እስካሁን ውጤቱን አላሳወቀም። የሚደራደረው ኮሚቴም ይሄ ነው። ውጊያ ሲመጣ ለሕዝብ አሳውቀን የጀመርን ሰዎች፣ ድርድር ከተጀመረ የሚያስደብቀን የለም። ነገር ግን የብቻ ጠላት የለም የሀገር ጠላት እንጂ፤ ለብቻም የሚሰራ ሥራ የለም በጋራ እንጂ። የእኛም የሕዝባችንም ፍላጎት ለጥይት የሚወጣ ውጪ ለልማት እንዲወጣ ነው። ሰላም እንፈልጋለን ማለታችን የተደበቀ ድርድር እናደርጋለን ማለት አይደለም” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በብዙዎች የለውጡ ጉዞ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሆኗል ስለመባሉና በለወጡ አሁናዊ ሁኔታ ዙሪያ ምን እየተደረገ እንደሆነ የምክር ቤት አባላቱ ለጠየቋቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በትክክል መገንዘብና ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። ኮቪድ፣ አንበጣ፣ ጎርፍ፣ ድርቅ ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች የራሳቸው የሆነን እንቅፋት ይዘዋል። በሀገር ውስጥ የገጠመን ውጊያም ከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል። መፈናቀል እና ያልተገባ የውጪ ጫናም ገጥሞናል” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ዓለም አቀፋዊ ጫናውም ለለውጡ ተግዳሮት መሆኑን አክለዋል፡፡ “የሀገር ውስጡ ሁኔታ ጋብ ሲል የዩክሬን እና የሩሲያ ግጭትም ያስከተለው ዓለም አቀፍ ጫና ተጋፋጭ ሆነናል። የገጠሙንን ፈተናዎች እንዴት አለፍናቸው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። የተደረገው ውጊያ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የመታደግ ሥራ እንደነበር ሊታወስ ያስፈልጋል። ለብልጽግናም መሰረቶችን ጥለናል። ይህ ሁሉ ፈተና እንደ መንግሥት፣ እንደ ፓርቲ በወጉ ሳንደራጅ የገጠመን ችግር መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል”ብለዋል፡፡
በመሰረተ ልማት ጉዳይ ለተነሳላቸው ጥያቄ መንገድን በአብነት በመጥቀስ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የገነባው መንገድ 13 ሺህ ኪ.ሜ. ብቻ ነበር። ባለፈው ሦስት ዓመት 4 ሺህ ኪ.ሜ. አስፋልት መንገድ ተጠናቋል። ከ9 ሺህ በላይ ኪ.ሜ ደግሞ በጀት ተመድቦለት በጸጥታ ምክንያትና በሌሎች ምክንያቶች ሥራው ተጓትቷል። 22ሺህ ኪሜ ርቀት ያለው መንገድ እየተጠናቀቀ ይገኛል” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት “በአዲስ አበባ 151 ኪ.ሜ አስፋልት አንዳንዱ እስከ 60 ሜትር ስፋት ያለው፣ 470 ኪሜ ኮብል ስቶን ንጠፎች እና 116 ኪሜ ሰፋፊ የእግር መንገዶች ተገንብተዋል። የትራፊክ ማሳለጫዎች ተሰርተዋል። ከሳር ቤት ጎተራ የመጀመሪያው ረዥም የመንገድ ውስጥ መተላለፊያ በ2 ዓመት ተኩል በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ የፓርላማ ማብራሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕድገት ሌላኛው ጉዳይ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት“አየር መንገዱ ከኮሮና በኋላ 35 በመቶ የአውሮፕላኖች ጭማሪን አሳይቷል። ወደ 127 መዳረሻዎች ይበራል። 3.3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ያስገኝ የነበረው ወደ 4.8 ዶላር ገቢ አድጓል። 6 ቢሊየን መንገደኞችን በአንድ ጊዜ ያስተናገድ የነበረ ሲሆን አሁን የማስተናገድ አቅሙም ወደ 22 ቢሊየን አድጓል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቴሌኮም ዘርፍ ተመዘገበ ያሉትን ስኬትም ለምክር ቤቱ አባላት ገልፀዋል፡፡ ጠቅላዩ እንዳሉት “የደንበኞች ብዛት ከ38 ሚሊየን ወደ 65.5 ሚሊየን አድጓል። ትርፉ ከ33 ቢሊየን ብር ተነስቶ 21.5 ቢሊየን ብር ጭማሪ አሳይቷል። ለተጠቃሚዎች ዋጋ ቀንሶ ገቢው ጨምሯል። በግጭት ምክንያት የአገልልሎት ሽፋን የማያገኙ ተቋማት አሉ። ሁሉን አልደረስንም፤ ገና ነን ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል። ውጤት መጥቷል ነገር ግን ወደምንፈልግበት ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀረናል” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስኳር ምርት ከ200 ሺህ ወደ 360 ሺህ ቶን አድርጓል ያሉ ሲሆን የትምህርት ጉዳይንም አንስተዋል፡፡ በእሳቸው ማብራሪያ መሰረት “15 ሺህ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ተካሄዷል። 1.7 ሚሊየን ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ በትምህርት ቤት ምገባ ድጋፍ ያገኛሉ” ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ታምርት” የተሰኘ ንቅናቄ በቅርቡ ተጀምሯል ያሉት ዶ/ር አብይ “ከለውጡ በኋላ 3 የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያዎች እና 9 ኢንደስትሪያል ፓርኮች በድምሩ 12 የኢንደስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል። የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ (AGOA) እንኳን ቀርቶ የውጪ ንግድ አድጓል። ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት ሥራም ተሰርቷል” ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል የግብርና ዘርፉን የማዘመን ሥራዎችንም መንግስታቸው እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
“የኩታ ገጠም ግብርና 45 በመቶ ደርሷል። ለግብርና የሚሰጠው የብድር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። ዘንድሮ ብቻ መንግሥት ለማዳበሪያ 15 ቢሊየን ብር ደጉሟል። ስንዴ በገፍ ስላመረትን ኤክስፖርት ማድድግ በቅርቡ እንጀምራለን” ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ላይ 628ሺህ ተማሪ በቀን ሁለቴ እንመግባለን ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ልጆቻቸውን ከትምህርት እንዳያቋረጡ፡፡ ያ አይበቃም ብለን በ6 ማእከላት በቀን አንዴ የማይመገቡ ሰዎች በነፃ የሚመገቡበት 6 ማእከላት ገንብተን በነፃ ይመገባሉ ሰዎች፡፡ ሄዳችሁ ማየት አለባችሁ፤ ስጠይቅ አልመጡም ስለተባለ ማለት ነው፡፡ አሁን ተጨማሪ 6 ማእከላት እየገነባን ነው፡፡ አንዴ የማይበሉ ሰዎች ሄደው እንዲበሉ፡፡
ማዕድ ማጋራት በሃገር ደረጃ እናንተን ጨምሮ ብዙ ደጋጎች ባደረጉት እርዳታ፤በጣም በርካታ ሰዎች በልተው ማደር ችለዋል፡፡ ማእድ ማጋራት በጀት ውስጥ አይታይም በኢንፍሌሽ ውስጥ ግን ትርጉም አለው፡፡ ምግብ የሚቸገሩ ሰዎች ምግብ እንዲያገኙ እድል ይሰጣል፡፡
የኑሮ ውድነትን በተመለከተም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም የምግብ ዋጋ ጭማሪን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ “ዳቦና ፋብሪካን አቅም ከፍ ያደረግነው እኛ ነን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በድምሩ 20 ምናምን ሺህ ዳቦ ብቻ ነበር የሚመረተው፡፡ በጀመርነው ሪፎርም ሸገርና ብርሃን (በሼህ መሃመድ አላሙዲንና የቀዳማይ እመቤት አማካኝነት የተቋቋሙት ዳቦ ፋሪካዎች) ብቻ ከ2 ሚሊየን ዳቦ በላይ በቀን ይጋግራል፡፡ ያ አልበቃ ብሎ አዲስ አበባ ውስጥ 10 ተጨማሪ ፋብሪካዎች ተገንብተዋል፡፡ በአሀኑ ወቅት አብዛኛዎቹ ሙከራ እያደረጉ ነው፡፡ በአጠቃላይ 3.4 ሚሊየን ዳቦ የመጋገር አቅም ተፈጥሯል አሁን በአዲስ አበባ” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ “ተረኝነትም” ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት “ሀገራችን ለሁላችንም የሚበቃ ሀብት አላት። የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህል እና ከምንም በላይ የጊዜ ሀብት አለን። ይህን ሰብስቦ ለጥቅም ማዋል ሲቻል ሀገርን እንደ እቁብ አይቶ በዚህኛው ቀን ለእከሌ፣ በሌላ ቀን ለእከሌ በፈረቃ የምትደርስ ያደርጋታል። እንኳን ለሀገር፣ ለመብራትም ፈረቃ ይከብዳል።
ሀገር የምትመራው በጋራ ነው። ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ርዕሰ ብሔር የሀገረ መንግሥቱ ምሰሶዎች ናቸው” ናቸው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምክር ቤቱ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ወስዶ የብሔር፣ የጾታ፣ የእምነት እና የመሳሰለውን ተዋጽዖን የተመለከተ ሕግ አውጥቶ በዚያ መሠረት ቢያስፈጽም የሚነሳውን ጥያቄ ሁሉ በሚገባ ይቀርፈዋል” ያሉ ሲሆን “የምናነሳው ሀሳብ ሁሉ በእውነታ እንጂ በተረት ላይ የተመሰረት አይሁን” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል “ህግ የማስከበር ዘመቻ” በሚል በመንግስት እየተወሰደ ያለውን አነጋጋሪ እርምጃ በተመከለተም የምክረ ቤቱ አባለት ጥያቄ አንስተው ዶ/ር አብይ ምላሽ ሰጥዋል፡፡ "ፋኖ ለኢትዮጵያ ተዋግቷል ወደ ፊትም ይዋጋል፡፡ ይህን ስም ለማያስፈልግ ተግባር ግን መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡ ፋኖ ለአማራም ለኢትዮጵያም ኩራት ነው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ በጀግንነት ተዋግቷል፡፡ በጀግንነት ይዋጋል ወደፊትም። በከተማ ተኩስ ብቻ ሳይሆን መዝረፍ፣ ሴቶችን መድፈር፣ ህፃን መጥለፍ፣ ነጋዴ መዝረፍ፣ ግብር መሰብሰብ ፎርጅድ ብር ማምረት ይሄ የፋኖ ስራ ሊሆን አይችልም"ሲሉ የእርምጃውን ምክንያት ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በአማራ ክልል በተወሰደው እርምጃ የፌደራል መንግሥት ሳይሆን የክልሉ ልዩ ኃይል ነው የተሳተፈው” ያሉ ሲሆን “የየክልሉን የሕግ ማስከበር ዘመቻ የሚመራው የክልሉ ኃይል ነው፡፡ ከፌደራል የሚያገኘው የቴክኒክ ድጋፍ ብቻ ነው” ሲሉ በእርምጃው መንግስታቸው ጣልቃ እንዳልገባ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ አካባቢያዊ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃው በሕዝብ ጥያቄ እንደተጀመረ በተገኘው ውጤት ሕዝብ ደስተኛ መሆኑን እና ሰላም እያገኘ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል። “በሀገር ወዳዶች ስም የሚቆሙ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ግዴታ ነው። በክልሉ በሕግ ማስከበር እርምጃ 3 ሺህ 5 መቶ የከዳ ሰራዊት ተይዟል፡፡ ከዚሁም ውስጥ ከ2ሺህ የሚበልጠው ከልዩ ኃይል የወጣ ነው” ብለዋል ለምክር ቤቱ አባላት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ለምክር ቤቱ አባላት “በስህተት የተያዘና ያለአግባብ የተጎዳ ሰው ሊኖር ይችላል። ተጣርቶ የእርምት እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
(ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ)

