"ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችባቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ከአዲስ አበባ እንዲሰረዙ ጫና እየተደረገ ነው" አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

*** አዲስ አበባ የምታስተናግደው የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ኅብረት ጉባኤ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወር፤ በ2022 በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤም ሌላ አፍሪካዊ አገር እንዲያስተናግደው ጫናና ማግባባት እየተደረገ ነው፡፡

Homeland Report

Dina Mufti, spokesman of the Ethiopian Foreign Ministry. Source: Getty

ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችባቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ከአዲስ አበባ እንዲሰረዙ ጫና እየተደረገ ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፤ እየደረሱ ባሉ ውድመቶችና ጉዳቶች የዓለም አቀፍ ተቋማት ዝምታንም ኮንነዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት “አንዳንድ የውጭ ሀገራት ቀደም ሲል በሰላም ሀገር ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ሲያደርጉት የነበረው ውትወታ ሲከሽፍ በሌላ አቅጣጫ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ ነው “ ብለዋል፡፡

አምባሳደር ዲና “ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችባቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የሚከናወንበት ቦታ ከአዲስ አበባ እንዲሰረዝ ሌሎች ሀገራትን እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ማግባባት መጀመራቸውን” ወቅሰው ለአብነትም በፈረንጆቹ ሰኔ ወር አዲስ አበባ የምታስተናግደው የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ጉባኤ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወር ጫና እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አክለውም በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት 2022 በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤም ሌላ አፍሪካዊ ሀገር እንዲያስተናግደው ለማግባባት እየሞከሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትን አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን በተመለከተ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ እየተጠቀሙበት” መሆኑንም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡ አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የጤና ተቋማት “በአሸባሪው ሕወሃት” ሲወድሙ ከማውገዝ ይልቅ ዝምታን መምረጡ አንዳሳዘናቸውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ቃልአቀባዩ “ድርጅቱ ለጤና ተቋማት በግንባር ቀደምትነት መሟገትና መከራከር የሚገባው ተቋም ቢሆንም የተከሰቱትን ውድመቶች በዝምታ ማለፉ አሳዛኝ ነው” በማለት ነው የገለጹት። በተመሳሳይ የተ.መ.ድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የላልይበላን ቅርስ ደኅንነት በተመለከተ በዚህ ወቅት ምንም አለማለቱ አስገርሞናል ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

በአፋርና በአማራ ክልሎች ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ ሲዳረጉ የዓለም ምግብ ድርጅት ዝምታን መርጧል ያሉት አምባሳደር ዓለም አቀፍ ተቋማቱ የተነሱበትን መርህ ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያራምዱት አቋም አድሏዊነት የሚስተዋልበት መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ግብጽ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ቱርክ ተጉዘው በኢትዮጵያ ጉዳይ መምከራቸውና መልዕክተኛው ወደ ሶስቱ አገራት ጋር የመከሩባቸው አጀንዳዎችን ኢትዮጵያ ታውቃለች ወይ? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ዲና “ጄፍሪ ፊልትማን ከሶስቱ አገራት ጋር በምን ጉዳይ እንደመከሩ መረጃ የለንም” ብለዋል።

አዲስ አበባ ያሉ አንዳንድ ኢምባሲዎች ዜጎቻቸው አሁንም ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ስለመቀጠላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ምን እየሰራ እንደሆነም ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ አምባሳደር ዲና “ ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነው” ሲሉ በአጭሩ መልሰዋል።

 


2 min read

Published

Updated

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now