የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትናንት ባወጣው መግለጫ በእስር ላይ የሚገኙት ታምራት ነገራ፣ ክብሮም ወርቁ፣ መዓዛ መሃመድ እና የእያስፔድ ተስፋዬን ጉዳይ ለማጣራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን የገለጸ ሲሆን በተለይም ታምራት ነገራ በፖሊስ ከተያዘበት ከታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ያለበት ቦታ አለመታወቁ እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ አክሎም ከጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር የቆየው ክብሮም ወርቁ በኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ከተፈቀደለት ጊዜ ጀምሮ ኢሰመኮ ይህን መግለጫ እስካወጣበት ጊዜ ድረስ የተያበበት ቦታ ለቤተሰቦቻቸው አልተነገረም ብሏል፡፡
በዚህም ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞች የቤተሰብ ጥየቃ መብታቸው ያልተከበረላቸው ከመሆኑም በላይ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁ ኮሚሽኑን እንዳሳሰበውና በአስቸኳይ ግዜ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ታሳሪዎች ያሉበት ሁኔታ ሊታወቅና በቤተሰብ እና በሕግ አማካሪ የመጎብኘት መብቶች ሊጣሱ አይገባም ብሏል፡፡
በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ሁለቱም ታሳሪዎች የሚገኙበትን ቦታ በአስቸኳይ ለቤተሰቦቻቸው እና ለሕግ አማካሪያቸው እንዲያሳውቁና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብታቸውን እንዲያረጋግጡ ኢሰመኮ አሳስቧል፡፡
አያይዞም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰብአዊ መብቶችን መርሆች ባከበረ መልኩ መተግበሩን የሚመለከታቸው አካላት በቅርብ ሊከታተሉ እና ሊያረጋግጡ እንደሚገባም ጥሪ አቅርቧል፡፡

