የኢትዮጵያ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚመረምር አንድ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን እንዲቋቋም ያሳለፈው ውሳኔ የተወሰኑ ፖለቲካዊ ተነሳሽነትን ያቀፈ አጀንዳ ለማራመድ በመሆኑ ያደረበትን ቅሬታ ገልጦ ውሳኔውን እንደማይቀበለው ዲሴምበር 17 ባወጣው መግለጫ አስታወቋል።
መንግሥት በተደጋጋሚ ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ከማካሄድ ይልቅ ገንቢ በሆነ የትብብር መንፈስ አሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመሥራት መጠየቁን፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዲሴምበር 14 2021 ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ፕሬዚደንት በኢሰመኮና የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ ምርመራ ምክረ ሃሳቦች በሁሉም የምክር ቤቱ አባላት እንዲተገበሩ የቀረበውን የተጻረረ መሆኑንንም ጠቅሷል።
አክሎም ድርጊቱ በተወሰኑ ምክር ቤት ውስጥ ባሉ በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ ለመግባት አማራጭ መንገዶችን መፈለጊያ እንደሆነ አመላክቶ ይህም ምድር ላይ ያለውን ሁኔታ ከማባባስ በስተቀር የሚፈይደው ነገር እንደሌለ አስገንዝቧል።
መግለጫው አያይዞም፤ ኢትዮጵያ ከፈቃዷ ውጪ ለተጫነባት ውሳኔ ትብብር እንደማታደርግ ደግማ ማሳሰብ እንደምትሻ አስታውቋል። ለኢትዮጵያ ድጋፍና አጋርነታቸውን ላሳዩ ሁሉ መንግሥት ምስጋናውን አቅርቧል።
ዲሴምበር 17 በተካሔደው ልዩ ስብሰባ ወቅት የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመረምር ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲቋቋም በተሰጡ ድምጾች 21 አገራት የድጋፍ 15 ተቃውሞ 11 አገራት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል። የሚቋቋመው ኮሚሽን የአንድ ዓመት የሥራ ዕድሜ ያለው ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱም ሊራዘም ይችላል።

መርሳና ግራና
መርሳና ግራና በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት ቁጥጥር ስር መሆናቸውን መንግሥት አስታወቀ።
በዚህም መሠረት፤
- በራያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉ ከፍተኛ ቦታዎች
- የውርጌሳ፣ የሊብሶ፣ የግራና፣ የመርሳ፣ የኪሌ ከተሞችን
- በሰሜን ወሎ የሐርቡ ወረዳ ከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራሮች በመንግሥት እጅ ገብተዋል።
በሕወሓት በኩል የኢትዮጵያ አየር ኃይል በድሮን በፈጸማቸው ጥቃቶች የሰላማዊ ሰዎች ሕይወቶች መጥፋታቸው ሲመለከት፤ መንግሥት በበኩሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በውጫሌና ውርጌሳ መካከል የነበሩ የሕወሓት ተዋጊዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጧል።

