የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ረፋድ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳረጋገጡት ኢትዮጵያና ቱርክ የውኃና መከላከያ ትብብር ስምምነቶችን ተፈራርመዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ቱርክ አቅንተው በፕሬዝደንቱ ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንና መንግሥታቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ያላቸውን የላቀ አክብሮት በገለፀ መልኩ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋልም ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ኢትዮጵያና ቱርክ የረጂም ዘመን ወዳጅነት አላቸው ያሉት አምባሳደር ዲና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱርክ ጉዞ እጅግ የተሳካ ጉብኝትና ውጤት የተገኘበት ነበር ብለዋል።

በሌላ በኩል ምክትናል ጠቅላይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት ከጄፍሪ ፊልትማን ጋር መወያየታቸውን የገለፁት ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ችግር ስረ መሰረት በሰፊው ተወያይተዋል ብለዋል።
በውይይታቸው በተለይም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ "አሜሪካ አቋሟ ሚዛናዊ እንዳልሆነና አሸባሪውን ሕወሓት የደገፈ መሆኑን ፣ በቅርቡ የተከናወነውን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫም እንደምንም መቁጠር፣ በኢትዮጵያ መንግስት የተወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ዕውቅና አለመስጠት ፣ አስቀድሞ በማይካድራ በቅርቡም በአፋር በሕወሓት የተፈፀመውን ጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀሎች ማውገዝ እንዳፈሩ፣ በአፋርና በአማራ ክልል አሸባሪው ሕወሓት ወረራ መፈፀሙን አለማውገዝና የመሳሰሉትን" የኢትዮጵያን መንግስት ቅሬታዎች በግልፅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስረዳታቸውን ገልፀዋል።
ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ብሔራዊ ንግግር ቁመና ያለበትን ደረጃም አስረድተዋል ብለዋል።
የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማንም የአሜሪካን አቋም ገለፀዋል ያሉት አምባሳደር ዲና " እኛ ለኢትዮጵያ ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ያለን አቋም ግልፅና ፅኑ ነው፣ ኢትዮጵያ በቀጠናው ወሳኝ ሚና ያላት አገር ነች ፣ እኛም ለሰላም ያለን ትኩረት ነው ብዙ ነገሮችን በትኩረት እንድንከታተለው እያደረገን ያለው። የሰሜኑ ጉዳይም በሠላም እንዲፈታ እንፈልጋለን" ማለታቸውን ገልፀዋል።
ፊልትማን ሠላማዊ ንግግር አድርጉ የሚል መልዕክት ይዘው መምጣታቸውን ፣ በቆይታቸውም ከሰላም ሚኒስቴር ኃላፊዎችና ተጠሪ ተቋማቱ ጋር ይገናኛሉ ብለዋል ቃል አቀባዩ።
አምባሳደር ዲና በቅርቡ ይፋ የተደረገውና በትግራይ ጉዳይ ያተኮረው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ " የመረጃ ምንጩ የአንድ ወገንና ገለልተኛ ያልሆነ መግለጫ" ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
"አሸባሪው ሕወሓት" ለቅርሶች በተለይ ለላሊበላ ስጋት መሆኑን፣ 300 ሺህ ወገኖችም በሕወሓት ወረራ ከአፋርና አማራ ክልል መፈናቀላቸውን ገልፀዋል።
በዛሬው መግለጫቸው እንዳሉት ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ መከላከያ ጎን መሆናቸውን በሰልፍና በገንዘብ ድጋፍ እየገለፁ መሆናቸውንና መንግስታቸው የሚያመሰግነው ድርጊት መሆኑንም ገልፀዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]

