የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎችና ሌሎች ተዋናዮች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በሕግ የተደነገገው የጊዜ ገደብ እስከሚያበቃበት ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ብቻ እንደሚቀበል አስታውቋል።
ቦርዱ በሰጠው ዕለታዊ መግለጫ፣ በግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው 7ኛው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች በሕጋዊ ሥርዓቱ መሰረት ተቀብለው እንደሚታዩ ገልጿል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ እንደገለጹት፣ እስካሁን ባለው ጊዜ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ “ምርጫው ተጭበርብሯል” በማለት ለቦርዱ ቅሬታውን ማስገባቱን አረጋግጠዋል። የፓርቲው አቤቱታም በቦርዱ የሕግ ክፍል እየተመረመረ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰብሳቢዋ አክለውም ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በምርጫው ዙሪያ የሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች በሕግ እስከተወሰነው ቀነ-ገደብ ድረስ እንደሚቀበሉ እና በሕጋዊ አግባብ ተጣርተው ተገቢው ውሳኔ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።
ቦርዱ ባወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ የቅሬታ ማቅረቢያ ጊዜ ገደብ ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም የሚያበቃ መሆኑንም ገልጿል።
ሜላተወርቅ ኃይሉ፣ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ ሂደት መጠናቀቁንና ውጤቶች መለጠፋቸውን ተናግረዋል።
አያይዘውም ከምርጫ ጣቢያዎች የተሰበሰቡ የድምፅ መረጃዎችን በምርጫ ክልሎች ደረጃ የማዳመር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ በምርጫ ክልል ደረጃ የተጠናቀቁ ውጤቶችን ወደ ቦርዱ ማዕከል የማስገባት ሂደትም መጀመሩን ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
ቦርዱ በአሁኑ ወቅት የምርጫ ውጤቶችን በማጠናቀር ላይ እንደሚገኝ ሲገልጽ፣ የመጨረሻ ውጤቶች ሕጋዊ የቅሬታ ሂደቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ይፋ እንደሚደረጉ ጠቁሟል።

