የኢትዮጵያ መርከብ ከ23 ዓመታት በኋላ በሞምባሳ ወደብ አገልግሎት መስጠት መጀመሯን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት(ኢባትሎአድ) አስታወቀ።
ድርጅቱ የአፍሪካ ሀገራትን በንግድ የማስተሳሰር ሥራን በ2010 ዓ.ም መጨረሻ የኤርትራን ጭነት ከምጽዋ ወደብ ወደ ቻይና በማጓጓዝ የጀመረውን አገልግሎት በማስቀጠል ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሶማሌላንድ በበርበራ እና በግብጽ በሳፋጋ እና ፖርት ሳይድ ወደቦች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ “ጊቤ” የተሰኘችው የኢትዮጵያ መርከብ የኬኒያን ጭነት ከኦማን ሱሐር ወደብ በመጫን ሞምባሳ ወደብ ገብታ በማራገፍ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል።
ከዛሬ 23 ዓመታት በፊት “አድማስ” የተባለችው መርከብ ወደ ሞምባሳ ካደረገችው የመጨረሻ ጉዞ በኋላ የጊቤ መርከብ በሞምባሳ መገኘት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።
የኢትዮጵያ መርከቦች የገቢ ወጪ ጭነት ከማጓጓዝ በተጨማሪ በቀጠናው ላሉ አገራት አገልግሎት በመስጠት ተደራሽነታቸውን እያሰፉና ተጨማሪ ገቢ እያስገኙ ነው ብሏል።
“ኢባትሎአድ አፍሪካን ከሌላ አህጉር በንግድ የሚያገናኝ የመጀመሪያው እና ብቸኛው አፍሪካዊ የመርከብ ኩባንያ መሆኑን ቀጥሏል” ያለው ድርጅቱ “ብሔራዊ የንግድ መርከባችን ከአፍሪካ ብቸኛው የአገርን ሰንደቅ ዓላማ በባሕር ላይ የሚያውለበልብ ሆኖ በመቀጠል የኢትዮጵያ ኩራት ሆኗል” ሲል ገልጿል።
ኢትዮጵያ ዘጠኝ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡና ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች አላት፤ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡት መርከቦች በተመሳሳይ 28 ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያላቸው መሆኑን ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመክታል።
ሁለቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እያንዳንዳቸው 40 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ የማንሳት አቅም ያላቸው ናቸው።