አብን በምዕራብ ወለጋው ጥቃት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ወቀሰ

*** የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ ተበተነ

News

Members of the House of People's Representatives. Source: Getty

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቀበሌዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን “የዘር ማጥፋት ወንጀል" አስመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወሰደው አቋም የተጣለበትን ኃላፊነት የማይመጥን ነው ሲል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ።

አብን ባወጣው መግለጫ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስቸኳይ አጀንዳዎችን የማስተናገድ ሕጋዊ ስልጣን የተሰጣቸው ቢሆንም የአብን አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ያቀረቡትን አስቸኳይ አጀንዳ አለመቀበላቸው አሳዛኝ ነው ብሏል።

በተጨማሪም ብሔራዊ የደህንነት ስጋት የሆነውን የዘር ማጥፋት ወንጀልን በሚመለከት አብን ያነሳውን ጉዳይ “ተራ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ” ሲል ፓርላማው መሳለቁ ምክር ቤቱ የተጣለበትን አደራ ያጎደለ ነው ብሏል ፓርቲው።

ምክር ቤቱ አሁንም ወንጀሉን ጉዳዩ በማድረግ እንዲወያይበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ ሕዝብ ላይ ሳያቋርጥ እያሰለሰ የቀጠለውን የዘር ፍጅት ወንጀል ለማስቆም ያልቻሉበትን እና የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ተፈናቃዮች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረስ ያልቻሉበትን ምክንያት በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርበው እንዲያስረዱ እንዲታዘዙ እንዲሁም አደጋውን መከላከል የሚቻለው የዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ብሔራዊ ፖሊሲ ፣ ስትራቴጂ ፣ ሕግ እና አሰራር እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርቧል።

ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ምክር ቤቱ የጅምላ ግድያውን አጀንዳ እንዲያደርገው ቢጠይቁም ባለመደረጉ የአብን የምክር ቤት አባላት ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ምክር ቤቱ በትላንትናው እለት ጉዳዩን በተመለከተ በማህበራዊ ገፁ የ “ፓርላማ ስብሰባ ተራ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ” አይደለም ሲል ምላሽ መፃፉ ይታወሳል።

በሌላ ዜና ዛሬ ረፋዱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የደረሰውን ጭፍጨፋ ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

ተማሪዎቹ ከስድስት ኪሎ ካምፓስ ተነስተው ወደ አምስት ኪሎና አራት ኪሎ ተቃውሞ እያሰሙ ቢጓዙም ፖሊስ ሰልፉን በትኖታል። የአይን እማኞች ለኤስ ቢ ኤስ እንደገለፁት ፖሊስ በሰልፈኞቹ ላይ ድብደባ ፈፅሟል።

[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]


2 min read

Published

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now