"ሱፐርስፖርት ልዩ" የተሰኘ አዲስ የስፖርት ቴሊቪዥን ስርጭት ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀመረ

*** የ DSTV አቦል ቴሌቪዥን አንደኛ ዓመት ክብረ በዓልም ተከብሯል፡፡

News

Source: SBS Amharic

ሱፐርስፖርት ዲኤስቲቪ የስፖርት ይዘቶችን ለኢትዮጵያውያን በአማርኛ የሚያቀርብ "ሱፐርስፖርት ልዩ" የተሰኘ ቻነልን በይፋ ስራ አስጀመረ

የኢትዮጵያውያንን ስፖርት አፍቃሪያን ተደራሽ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የስፖርት ይዘቶች በሱፐርስፖርት/ዲኤስቲቪ የሚያቀርብ “ሱፐርስፖርት ልዩ” ቻነል 240 ትናንት በይፋ የስፖርት፣ ባህል፣ ሚዲያና ኪነጥበብ የመንግስት ኃላፊዎችና ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት በሀያት ሪጄንሲ ሆቴል ተመርቋል፡፡

በዕለቱ የዲኤስቲቪ አቦል ቴሌቪዥን አንደኛ ዓመት ክብረ በዓልም ተከብሯል፡፡

የመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ የሬጉላቶሪና ኮርፖሬት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መታሰቢያ በላይነህ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ለአቦል ቤተሰቦችና የፊልም ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት ለአቦል አንደኛ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን፤ ለስፖርቱ ባለድርሻዎችም አዲሱ የሱፐርስፖርት ልዩ ቻናል240 ሥራ በመጀመሩ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

News
Metasebiya Belayneh. Source: SBS Amharic

አቶ መታሰቢያ የአፍሪካ ግዙፉ ስፖርትና መዝናኛ ይዘቶች አቅራቢው መልቲቾይዝ አፍሪካ በሚሰራባቸው አገራት የህዝብና የሀገር ገፅታ ፣ ባህልና ታሪክ ለዓለም እንዲደርሱ እየሰራ ነው ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ይህንኑ የሚያንፀባርቁ "አቦልና ሱፐርስፖርት ልዩ" የተሰኙ ቻነሎች ተከፍተዋል ብለዋል።

ከአማርኛ በተጨማሪም ኦሮምኛን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በስርጭት ጊዜ የመጠቀም ዕቅድ አለ ያሉ ሲሆን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በመመደብ ከአፍሪካ ሀገራት በላቀ መልኩ በኢትዮጵያ ለመስራት መልቲቾይዝ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

በዕለቱ የተገኙት የክብር እንግዳው የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደተናገሩት “ ስፖርት መዝናኛ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የልማት አንዱ ምሶሶ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ መንግስት የያዘችው ስትራቴጂ ስፖርት ለልማት የሚል ነው፡፡ በዚህ አግባብ ከመልቲቾይስ ጋር በትብብር እንሰራለን፡፡ በጀመርነው ልማትና አገራዊ የገፅታ ግንባታ ትክክለኛ ሚዲያ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በመሆኑም የድርሻችንን የምናግዝ ይሆናል፡፡ መልቲቾይስም ስፖርቱንና ባህሉን አስተሳስሮ የገፅታ ግንባታና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሰራ አደራ እንላለን፡፡” ብለዋል፡፡

News
Ambassador Mesfin Chernet. Source: SBS Amharic

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ ኢድሪስ በበኩላቸው “ዲኤስቲቪ ትናንት በአቦል የጀመረውን ዛሬ ደግሞ በሱፐርስፖርት ልዩ መምጣቱ አስዳሳች ነው፡፡ ዲኤስቲቪ ዓለምን ወደኛ እኛን ደግሞ ወደ ዓለም የወሰደ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለአፍሪካና ለዓለም ፤ ዓለምንና አፍሪካን ደግሞ ለእኛ በማስተዋወቅና በማስተሳሰር ትልቅ የገፅታ ግንባታ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ዲኤስቲቪ በዚህ ረገድ አይቻልም የተባለውን ችሎ ያሳየ ነው፡፡ በቀጣይ በሌሎች ተጨማሪ ቻናሎችና ቋንቋዎች እንደምናገኘው ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

News
Muhammed Idris. Source: SBS Amharic

ከመልቲቾይስ ጋር በትብብር ስምምነት የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ በሱፐርስፐርት/ዲኤስቲቪ አማካኝነት አህጉራዊ ስርጭት መሰጠቱ ያስገኘውን ጠቀሜታ በተመለከተ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ/ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ሰይፈ “ ዲኤስቲቪ ፕሪሚየር ሊጋችንን በፋይናንስ ከመደገፍ ባለፈ በአቅም ግንባታ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊዎች ሽልማት በመጠንና በዓይነት ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ዲኤስቲቪ የሊጋችንን የመታየት ዕድል በመፍጠሩ የነበረብንን ክፈተት እንድናውቅ ብቻም ሳይሆን ክፈተታችንን ለመሙላት ተግተን እንድንሰራ መነሳሳት ፈጥሮልናል፡፡” ብለዋል፡፡

News
Kifle Seife. Source: SBS Amharic

የዓለም የምንጊዜም ምርጡ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴም ሱፐርስፖርት ለስፖርቱ ያደረገውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመድረኩ ራሱን እንደምሳሌ በመጥቀስ መስክሯል፡፡ ኃይሌ “ እኔን ያደመቀኝ ሱፐርስፖርት ነው፡፡ በተከታታይ ሶስት ዓመታት ማለት በ1995፣ 1996 እና 1997 እኤአ የሱፐርስፖርት ኮከብ ተሸላሚ አትሌት ነበርኩ፡፡ እኔን በዓለም ላይ እንዳደመቃችሁኝ ሁሉ የአሁኑን የአትሌቲክስ ትውልድ ለዓለም እንድታስተዋውቁ አደራ እላለሁ” ብሏል፡፡

News
Haile Gebre-Selassie. Source: Getty

ሰርቢያ ቤልግሬድ የ2022 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶችን ከዓለም በአንደኝነት ማሸነፍ በአዲሱ ሱፐርስፖርት ልዩ በቀጥታ በአማርኛ መሰራጨቱን በተመለከተ በመድረኩ የተጠየቁት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሸቦ “ ዲኤስቲቪ ዓይናፋርነታችንን የሚገፍ በዓለም መድረክ ላይ አትሌቶቻችን ራሳቸውን የሚገልፁበት፣ ስለሀገራቸውና ስለአትሌክሱ የሚናገሩበት የሚዲያ አማራጭ በመሆኑ ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ዲኤስቲቪ በኢትዮጵያ ለእግር ኳሱ የነበረውን ትኩረት በአትሌቲክሱ በመድገም የቤልግሬድ የቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የቀጥታ ዘገባ በማስተላለፉ የሚያስመሰግን ስራ ሰርቷል፡፡ እኛም በጣም ደስተኞች ነን፡፡ በተጨማሪም ለሌሎች ስፖርቶችም የመታያ ሜዳ ይሆናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል፡፡

News
Commander Hussien Shebo (L). Source: SBS Amharic

በሌላ መልኩ የዲኤስቲቪ አቦል ቴሌቪዥንን አንደኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ልምዳቸውን ያካፈሉት አርቲስቶች አቦል ቴሌቪዥን ለኢትዮጵያ ፊልም ባለሙያዎች በፋይናንስና በተደራሽነት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

በሳምንት ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚተላለፈውን “አደይ” የተባለውን የመጀመሪያውን ቴሌኖቬላ ፕሮዲዩስ እያደረገ የሚገኘው አርቲስቲት ሰውመሆን ይስማው “አቦል ለፊልም ባለሙያዎች ዕድልም አቅምም ነው፡፡ ለምሳሌ በእኔ የረጅም ጊዜ የቀረፃ ልምድ ትልቁ በቀን የምንሰራው ስምንት ሲን ነበር። በኬንያ የሚገኝ ኩባንያ በቀን 35 ትዕይንቶችን መሥራቱን ስንሰማ ተገረምን በዚህም ቁጭት አድሮብን ተነሳን። በዚህ ቁጭታችን በቀን 36 ትዕይንቶች ሌት ተቀን ብለን በጥራት መስራት ችለናል። ይሄ አቦል ውጤት ነው። ዛሬ ላይ ልባችንን ሞልተን የምንናገረው ቢኖር በፕሮዳክሽን ጊዜ አጠቃቀም በጥራትና በጊዜ ለስርጭት በማስረከብ ውጤታማ እንድንሆን አስተምሮናል።" ብሏል።

News
Abol. Source: SBS Amharic

ጥላ የተሰኘ አዲስ የቴሌቪዥን ድራማ ይዞ በአቦል ብቅ ያለው አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን በበኩሉ " የዓለም የፊልም እይታ አማራጭ መስኮት እያደገ መጥቷል። የቴሌቪዥን ቻነሎች ለፊልም ኢንዱስትሪው ትልቅ አቅም ሆነዋል። እኛም በተበጣጠሰ መንገድ የምንሰራውን ስራ የተቀናጀ ሆኖ እንዲወጣ ዲኤስቲቪ አስተምሮናል። ተጨማሪ ዕድልም ሰጥቶናል። በማሳያነት በአሁኑ ሰዓት የአቦልን መምጣት ተከትሎ ብዙ የፕሮዳክሽን ኩባንያዎችና ወጣት የፊልም ሰሪዎች እየተፈጠሩ ነው። ፕሮዲዩስ የሚደረጉ የድራማ ፅሁፎችን ተደራጅተው የሚሰሩ ወጣቶች ተገኝተዋል። ይህንን ያደረገው ዲኤስቲቪ ነው።"

ወጣቷ የፊልም ፕሮዲዩሰርና ዳይሬክተር ኤደን ጌታቸው በቅርቡ በአቦል ቴሌቪዥን ለስርጭት ስለሚበቃው የባስሊቆስ እምባ እንደተናገረችው " አቦል ለእንደኔ ዓይነቱ አዲስ የፊልም ኢንዱስትሪ ዳይሬክተር እምነትን በማሳደር አዲስ ሰው እና አዲስ ፊት ለፊልም ኢንዱስትሪው አሻራ እንዲያስቀምጥ የፕሮዳሽን ስራዎች የፋይናንስ አቅምና የማሰራጫ ዕድል መፍጠር መቻሉ ትልቅ አስተዋፅኦ ነው" ብላለች።

በዕለቱ በርካታ የኪነ ጥበብ፣ ስፖርትና የሚዲያ ባለሙያዎች የታደሙ ሲሆን በአቦል የሚቀርቡ የአማርኛ ይዘቶች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የግርጌ የትርጉም ጹሑፍ (Subtitles) ታክሎባቸው ለዕይታ ይበቃሉ ተብሏል።

[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]


5 min read

Published

By Demeke Kebede



Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now