ጎንደር ከተማ ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት ግድያ ለተፈፀመባቸው ሰዎች ፍትሕ ተጠየቀ

*** የሟቾች ቁጥር 21 ደርሷል፤ የአማራ ክልላዊ መንግሥት በጥፋተኞች ላይ "ሕጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ" እወስዳለሁ ሲል አስታውቋል።

News

Friday prayer in the holy month of Ramadan at Anwar Mosque in Addis Ababa, Ethiopia on April 8, 2022. Source: Getty

በጎንደር ከተማ ሚያዝያ 18 በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ ግድያ የተፈፀመባቸው ስዎች ቁጥር 21 መድረሱ የአካባቢው የመረጃ ምንጮች አመለከቱ። 

በግጭቱ ሳቢያ ሕይወታቸው ላለፈ ሰዎችም ፍትሕ እንዲሰጥ በአዲስ አበባና አማራ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤቶች ተጠይቋል። 

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም በበኩሉ ድርጊቱን በብርቱ አውግዞ በጥፋተኞች ላይ አስቸኳይ እርምጃ እዲወሰድ ጠይቋል።   

የጎንደር የሃይማኖት ጉባኤ ተቋም በበኩሉ ግጭቱ የሁለቱንም እምነት ተከታዮች እንደማይወክል አስገንዝቧል።

ይህንኑ ለ21 ሰዎች ግድያ አስባብ የሆነውን ግጭት አስመልክቶም፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ዮሴፍ ደስታ ለአክባቢው ለአሚኮ እንደገለጡት "በጎንደር ከተማ የተከሰተው ግጭት ሰላምን በማይሹ፣ ለሰላም ዋጋ በማይሰጡ ሰዎች የተፈጠረ ችግር ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም፤ የጎንደር ወንጌላዉያን አብያተክርስቲያናት አገልጋይ አማን ሷሊህ "ግጭት ለማስነሳት የሞከሩ አካላት በእምነት ሽፋን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ለማራመድ የሚሹ ናቸው" በማለት ግጭቱ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል የተፈጠረ ተደርጎ እንዳይፈረጅ አሳስበዋል። 

በማከልም የሃይማኖት ጉባኤ ተቋሙ የሕይወትና ንብረት ውድመት ባደረሱ ግለሰቦች መንግሥት አስቸኳይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ግጭቱን ተከትሎ የደረሱትን የሕይወት ጥፋት፣ የንብረት ውድመትና የሰላም መደፍርስን አስመልክቶ በዕለቱ ሚያዝያ 18 የማረጋጊያና ተከታይ የሕጋዊ እርምጃ ወሰዳ ማሳሰቢያን ያዘለ መግለጫ አውጥቷል።

ክልላዊ መንግሥቱ የግጭቱን አነሳስና የደረሱ ጥፋቶችን አስመልክቶ "በዛሬው ዕለት የጎንደር ከተማ ነዋሪ እና የጎንደር ሕዝበ ሙስሊምና ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲሁም የኹሉም አባት የነበሩት ታላቁ ሸኽ ከማል ለጋስ ሥርዐተ ቀብር እየተፈጸመ በነበረበት ሰዓት ከቀብር ቦታው ጋር ድንበርተኛ የኾነው ቤተ ክርስቲያን ላይ ለቀብር የሚሆን ድንጋይ “እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው” በሚል በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል በተጀመረ ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ የአካል ጉዳትም ደርሷል። የተለያዩ ንብረቶችና ተቋማትን የማጥፋት እንቅስቃሴዎችም ተስተውለዋል" ሲል ገልጧል። 

አያይዞም፤ ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጦ፤ መፅፅናትንም ተመኝቷል። 

ለአካባቢው ሰላም መረጋጋትና ግጭቱ እንዲበርድ ለማድረግ አስተዋፅዖ ላደረጉ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የፀጥታ ኃይላትና ለከተማይቱ ነዋሪዎች ምስጋናውን አቅርቧል።

አክሎም "የአማራ ክልል መንግሥት በማንኛውንም አይነት የጽንፈኝነት አስተሳሰብ የሚፈጠር የሰላም መደፍረስንም ኾነ በንጹሐን ሕይወት፣ አካልና ሀብት ንብረት ላይ የሚደርስን ጥፋትን የሚሸከምበት ጫንቃ የለውም፡፡ ስለኾነም በጥፋተኞች ላይ አስፈላጊውን ኹሉ ሕጋዊ እና ተመጣጣኝ እርምጃም ይወስዳል" ሲል በአፅንዖት አስታውቋል።

የተወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎችንም በተከታታይ እንደሚያስታውቅ ቃል ገብቷል።   

 

 


2 min read

Published

By Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now