ማክሰኞ አመሻሽ 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ አንድ አነስተኛ አዉሮፕላን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ መዉደቁን የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት አረጋግጧል።
የኮምቦልቻ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብዲ ቡሽራ አራት ሰዎችን የጫነዉ አውሮፕላን ቄረንሳ ቀበሌ ተራራማ ቦታ ላይ መዉደቁን ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ከድሬደዋ ከተማ እንደተነሳና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ሰብአዊ አገልግሎት የሚል ጽሁፍ እንዳለበትም ተናግረዋል።
አውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ሶስቱ የኢትዮጵያ ዜጋ ሲሆኑ አንዱ የዉጭ ሀገር ዜጋ አንደሆነም አክለዋል። አደጋዉ የደረሰበት ቦታ አየር ሁኔታ በጣም ጭጋጋማ እንደነበር የተናገሩት አቶ አብዲ ቡሽራ የአደጋዉ መንስኤም ይኸዉ የአየር ሁኔታ ሊሆን እንደሚችል ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።
በረራው ወዴት እንደነበር የተጠየቁት አቶ አብዲ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ለ “ኢትዮጵያ ቼክ” የተናገሩ ሲሆን ግለሰቦቹ ይዘዋቸው የነበሩ ሻንጣዎችም እንደተገኙ አስረድተዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ባወጣው መግለጫ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታ አስተዳደር ስር የነበረና በረጂም ጊዜ ደንበኛው አቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ድርጅት አገልግሎት እየተጠቀሙበት እንደነበር ገልፆ ባልታወቀ ምክንያት ከጅግጂጋ ወደ ድሬደዋ ይበር እንደነበረ አስታውቋል፡፡
ሁለት የእርዳታ ሰራተኞችንና ሁለት የበረራ ሰራተኞችን የጫነ ቢሆንም አንዳቸውም የከፋ ጉዳት አላጋጠማቸውም ብሏል፡፡
የአደጋው ምክንያት እየተጣራ መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡
( ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ )

